የባለ '37A+' ውጤት ምሩቅ ቀለሜዋ- ሠብለወንጌል መንግስቱ - ኢዜአ አማርኛ
የባለ '37A+' ውጤት ምሩቅ ቀለሜዋ- ሠብለወንጌል መንግስቱ

የባለ '37A+' ውጤት ምሩቅ ቀለሜዋ- ሠብለወንጌል መንግስቱ።
ወርኃ ሠኔ ሲሰናበት፣ ሐምሌ ሲብት ተማሪ እና ትምህርት ቤት ለወራትም፤ ለዘመናትም ይፋታሉ።
በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቃን አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ለመጀመር በጎም፣ አሳዛኝም ትዝታ ከነበረበት የትምህርት ዓለም ወደ ሥራ ዓለም የሚቀላቀሉበት ጊዜ ነው።
በየዓመቱ የሚደረገው ሰሞነኛው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርቃት ላይ ከሁነቱ ባሻገር አዳዲስ አስገራሚ፣ አስደናቂ መልክ እና ክስተቶች ይስተዋላሉ።
ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ ጉርምስና የዘላቀ የተማሪነት ሕይወት ምዕራፍ ሲታጠፍ፣ ለተማሪዎች የትምህርትን ውጣ ውረድ ተወጥተዋልና የፌሽታ ስሜት ያጎናጽፋል።
የልጆቻቸውን ፍሬ ላዩ ወላጆች ደግሞ ዕፎይታ ይሰጣል።
ከሁሉም በላይ በትምህርት ዘመናቸው ትጉህ፣ ብርቱና ጽኑ ሆነው ፈተና ሳይበግራቸው፤ በልፋታቸው ያማረ ፍሬ ያፈሩ፣ የከፍተኛ ውጤት ሰቃዮች ወይም ቀለሜ ተማሪዎች በየዓመቱ የሰሚውን ቀልብ ይይዛሉ።
ከዘንድሮ ተደናቂ ቀለሜዎች መካከል የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በማኔጀመንት ትምህርት ክፍል ተመራቂዋ ሠብለወንጌል መንግስቱ አንዷ ናት።
ሠብለወንጌል በቆይታዋ ከወሰደቻቸው የትምህርት ኮርሶች መካከል 37ቱን "A+" (እጅግ በጣም ከፍተኛ) ውጤት በመደርደር ልዩ የማዕረግ ተመራቂ ሆናለች።
ሠብለወንጌል በሶስት ኮርሶች ብቻ "A-" ውጤት ስለነበራት 'ሙሉ አራት ነጥብ'(4:00) ማምጣት ባትችልም" አጠቃላይ አማካይ ውጤቷ(CGPA) 3 ነጥብ 99 በማስመዝገብ የዩኒቨርሲቲው የዋንጫ ተሸላሚ ናት።
አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው የሠብለወንጌል ቀለሜነት ከቅድመ መደበኛ(ኬጂ) ትምህርት ቤት የጀመረ ሲሆን ከአንደኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል የተማሪነት ዘመኗ በደረጃ ተማሪነት ቀጥላለች።
በ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና 99 በመቶ ፐርሰንታይል፣ በ10 ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና (ማትሪክ) ሁሉንም ትምህርቶች 'ኤ' (Straight-A) ውጤት በመያዝም ወደ ቀጣዩ ክፍል ተዛውራለች።
እንደሁም በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከ700 አጠቃላይ ድምር 545 ውጤት በማስመዝገብ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅላ ለዛሬው ስኬት በቅታለች።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረገችው ሠብለወንጌል እንደምትለው የስኬቷ ምስጢር ለትምህርት ሙሉ ጊዜ እና ትኩረት መስጠቷ ነው።
በተለይም "ከሁሉም በላይ በፈጣሪዬ ዕርዳታ ለዚህ ውጤት በቅቻለሁ" ትላለች።
በትምህርቷ ያስመዘገበችው ዕጅግ ከፍተኛ ውጤትም ከተመረቀችበት የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪ ነፃ ትምህርት ዕድል እንድታገኝ አስችሏታል።
ሠብለወንጌል ቀጣይ ሕልሟ አሁንም ያላትን ትጋትና ብርታት በመጽናት የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን ከዚህ በላቀ ውጤት የማጠናቀቅ ግብ ይዛለች።
ትምህርትን ካጠናቀቀች በኋላ ደግሞ በተመረችበት ሙያ ራሷ የምትመራው(ማኔጅ የምታደርገው) ኩባንያ በመመስረት፤ ለሀገርና ወገን የሚበጅ ቁም ነገር የመስራት ሕልም ሠነቃለች።
"የማይቻል ነገር የለም" የምትለው ሠብለወንጌል፤ የእርሷን አርዓያነት መከተል ለሚሹ ታዳጊዎች "ትምህርታቸው ላይ ብቻ ልዩ ትኩረት አድርገው ካጠኑ ውጤታማ ይሆናሉ" ስትል ትመክራለች።
ምሩቃኑ ደግሞ 'ባገኘነው የስራ ዕድል ሁሉ በመሰማራት በርትቶ መስራት በተለይም ስራ ፈጣሪ በመሆን ሕልማችንን መኖር ይገባናል' ስትል መልዕክት አስተላልፋለች።