ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ሆነ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ30ኛ ሳምንት መርሐ ግብር የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮጵያ መድንን 2 ለ 0 በማሸነፍ የሊጉን ዋንጫ አንስቷል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቀጣዩ ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ይሳተፋል።
የፕሪሚየር ሊጉን የዋንጫ አሸናፊ የሚለዩ ወሳኝ ጨዋታዎች ዛሬ በሃዋሳ ሁለት ሜዳዎች በተመሳሳይ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ተካሄደዋል።
በሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮጵያ መድንን 2 ለ 0 አሸንፏል።
ተከላካዩ ሱሌማን ሀሚድ በ3ኛው እና አጥቂው አዲስ ግደይ በ33ኛው ደቂቃ ለንግድ ባንክ የማሸነፊያ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ውጤቱን ተከትሎ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጣው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ64 ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን አንስቷል።
በ1990 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከተባለበት ጊዜ በኋላ ከታችኛው የሊግ እርከን በማደግ በመጣበት ዓመት የሊጉን ዋንጫ ያነሳ የመጀመሪያ ክለብም ሆኗል።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቀጣዩ ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ላይ ይሳተፋል።
ኢትዮጵያ መድን በ40 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዞ የውድድር ዓመቱን አጠናቋል።
በተመሳሳይ ሰዓት በሃዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ በተካሄደው ጨዋታ ሌላኛው የዋንጫ ተፎካካሪ መቻል ድሬዳዋ ከተማን 1 ለ 0 አሸንፏል።
አጥቂው ምንይሉ ወንድሙ በ6ኛው ደቂቃ ለመቻል ብቸኛዋን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ውጤቱን ተከትሎ መቻል በ63 ነጥብ 2ኛ ደረጃን ይዞ የውድድር ዓመቱን አጠናቋል።
ድሬደዋ ከተማ በ40 ነጥብ ተመሳሳይ የነጥብ መጠን ባላቸው ኢትዮጵያ መድንና ሲዳማ ቡና በግብ ክፍያ ተበልጦ 12ኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል።
ከመስከረም 20 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ ሲካሄድ የቆየው የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል።