ቀጥታ፡

ሰላምን የተመለከተ ሀገር አቀፍ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ነገ በኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2016(ኢዜአ)፦ሰላምን አስመልክቶ የተዘጋጀ ሀገር አቀፍ የ6 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ነገ በኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች እንደሚካሄድ የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ። 

ውድድሩ “ ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም!” በሚል መሪ ኃሳብ ይካሄዳል ተብሏል። 


 

የሩጫ ውድድሩ ነገ ከጠዋቱ 12 ሠዓት በተመሳሳይ በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋና በሌሎች ዋና ዋና የክልል ከተሞች ይከናወናል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ሩጫውን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ ሚኒስቴሩ ለውድድሩ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጎ አጠናቋል ብለዋል። 

የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሩ በመላው የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የሚሳተፉበት መሆኑን አመልክተዋል።

በአዲስ አበባ በሚካሄደው ውድድር ታዋቂ አትሌቶችና ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።

በሌሎች የአገሪቷ ከተሞች በሚደረጉ ውድድሮችም አትሌቶችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ እንደሚሆኑም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።

የሩጫው ዋንኛ ዓላማ ስለ ሰላም ግንዛቤ መፍጠርና ዜጎች ለዘላቂ ሰላም የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው የሚያሳስብ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሩጫው ከመሮጥ ባሻገር ዜጎች በኢትዮጵያ ሰላም ጉዳይ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እንዲወያዩ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል። 

ሰላም በአንድ ወገን ጥረት ብቻ የማይመጣ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላም መስፈን የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት። 

ጎን ለጎንም በቅርቡ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተደረጉ ውይይቶች ማኅበረሰቡ ካነሳቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ የሰላም መስፈን ነው ብለዋል።

መንግሥት የኅብረተሰቡን ጥያቄ በመቀበል ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ እየሰራ እንደሚገኝና ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም