በትግራይ ክልል የሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች በዘመናዊ የክፍያ ስርዓት አገልግሎት እንዲሰጡ ሊደረግ ነው

መቀሌ ፤ ሰኔ 29/2016(ኢዜአ)፦  በትግራይ ክልል የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ከሐምሌ  1 ቀን 2016 ዓ.ም  ጀምሮ  በዘመናዊ የክፍያ ስርዓት አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረግ ተገለጸ። 

ከተቀመጠው አሰራር ውጭ ሌላ አማራጭ የሚጠቀሙ ነዳጅ ማደያዎች ከተገኙ ከስራው እንደሚታገዱ ዛሬ በተሰጠው መግለጫ ተመልክቷል። 

መግለጫውን የሰጡት የትግራይ ክልል  የጊዜያዊ አስተዳደሩ የትራንስፖርትና መገናኛ ቢሮ፣ የጊዜያዊ አስተዳደር የንግድ ኤጀንሲ እና በኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ሪጅን ናቸው።

በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የንግድ ኤጀንሲ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ብቃት ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ክንደያ እንደገለጹት፤ ከሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ነዳጅ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችና  ጀኔሬተር ባለቤቶች የነዳጅ  ክፍያ ስርዓት በቴሌ ብር እንዲገለገሉ ይሆናል።

ዘመናዊ አሰራሩ በክልሉ በሚገኙ 60 ነዳጅ ማደያዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን አስታውቀዋል።

የነዳጅ መቅዳትና የክፍያው ስርዓት ዘመናዊ የማድረግ ስራ ነዳጅ በጥቁር ገበያ እንዳይሸጥ ለመከለከልና የተሳለጥ አገልግሎት እንዲኖር ለማስቻል መሆኑን ተናግረዋል።

በነዳጅ አጠቃቀም ዙሪያ የነበረው ህገ ወጥ ስራ ለግለሰቦች መበልፀገያ እንጂ ለህዝባችን የጠቀመ አይደለም ብለዋል።

ዘመናዊ የነዳጅ ግብይት አሰራር ተግባራዊ በማድረግ አገልግሎቱን የተቀላጠፈ  እናደርጋለን ያሉት ደግሞ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የትራንስፖርትና መገናኛ ቢሮ ሀላፊ አቶ ታደለ መንግስቱ ናቸው።

በኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ሪጅን ዳይሬክተር አቶ ሙሉ ወልደስላሰ በበኩላቸው፤ ነዳጅ  አሞላልና ክፍያ አፈፃፀም ላይ ያለው ኋላ ቀር አሰራር ተቀይሮ ፈጣንና ፍትሃዊ አገልግሎት በቴሌ ብር ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል። 

መብረት የመጥፋትና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ለመፍታት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም