ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ሽግግር ለማሳካት ዘመኑን የዋጀ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል-ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ሽግግር የሚያሳካ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት መንግስት ዘመኑን ለዋጀ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ልዩ ትኩረት መስጠቱን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ።

የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢኒስቲትዩት በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 2ሺህ 100 ተማሪዎችን አስመርቋል። 

በምረቃው ላይ የተገኙት የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ባስተላለፉት መልዕክት፥ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና እና ትምህርት ችግር ፈቺ፣ የፈጠራ ክህሎት እና ሀሳቦችን ያካተተ እንዲሆን ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሽግግርን ለማረጋገጥ ባለፉት አራት ዓመታት በተወሰዱ ክህሎት መር የፖሊሲ ማሻሻያ ትግበራዎች  ለውጦች መመዝገባቸውንም አስረድተዋል፡፡


 

ዘመኑን የሚመጥንና ጥራቱን የጠበቀ የቴክኒክና ሙያ ስልጠናን በመተግበር ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አንስተዋል።

ከመጪው ዓመት ጀምሮ በአዲሱ ፖሊሲ መሰረት በደረጃ 8 (ፒ.ኤች.ዲ) የቴክኒክና ሙያ ስልጠና እና  ትምህርት ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ዛሬ ከተመረቁት መካከል የጎረቤት ሀገራት ተማሪዎች እንደሚገኙ ጠቁመው፥ ይህም ኢትዮጵያ በቀጣናው  ትብብሯን በማጠናከር የተሻለ ነገን በጋራ ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ኢኒስቲትዩቱ እንደ ሀገር በክህሎት ልማቱ ዘርፍ አቅም እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፥ ክህሎት ጨብጠው የወጡ ሰልጣኞች ወደ ስራ መግባት ሀገራዊ የለውጥ ስራዎችን  ለማሳካት ተጨማሪ አቅም ይሆናል ብለዋል፡፡ 

ተመራቂዎች በትምህርትና ስልጥና ቆይታቸው ባገኙት እውቀት ሀገራቸውን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለመውሰድ እንዲያገለግሉም ጠይቀዋል።


 

የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር(ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ገበያ ተኮር መርህን በመከተል በሁሉም መስክ  ብቁ የሰው ኃይል እያፈራን ነው ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ በዲጅታል የታገዘ የስልጠና ስርዓትን ለመከተልና በዘርፉ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም