የህፃናትን የንባብ ባህል ለማዳበር ወላጆች የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት አለባቸው 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2016(ኢዜአ)፦የንባብ ባህልን በማዳበር ህፃናት ከመደበኛ ትምህርታቸው ባሻገር ዘርፈ-ብዙ ዕውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው ሊበረታቱና ሊደገፉ እንደሚገባ ተገለጸ። 

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር የንባብ ባህልን ለማዳበር የወላጆች ሚና ምን መሆን አለበት? በሚል ከደራሲያን ማኅበር አባላት ጋር በዛሬው ዕለት ውይይት አድርጓል።

የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ደራሲ አበረ አዳሙ፤ የህፃናትን የንባብ ባህል በማዳበር፣ ከመደበኛ ትምህርታቸው ባሻገር ዘርፈ-ብዙ ዕውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው እንደሚያግዝ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት በተሻለ ደረጃ ፍሬያማ እንዲሆን ልጆች ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ጠቅላላ ዕውቀትን የሚያዳብሩ መጻሕፍት እንዲያነቡ ወላጆች ሲያበረታቱ ነው ብሏል።

በኢትዮጵያ የንባብ ባህል በሚፈለገው ደረጃ አለመገንባቱን የገለጸው ደራሲው፤ ለዚህም ከታች ጀምሮ ባለመሠራቱ መሆኑን ነው የገለፀው። 

በመሆኑም ወላጆች ይህንን ለመቀየር ልጆቻቸው አንባቢ እንዲሆኑ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ምክረ- ሃሳባቸውን ሰጥቷል።  

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፀሐፊ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በበኩሉ፤ ወላጆች ልጆቻቸው አንባቢ እንዲሆኑ አርዓያ መሆን አለባቸው ብሏል። 

ወላጆች የንባብ ልምድ ውስጥ ያላለፉ ከሆኑ ደግሞ፤ ቢያንስ የመጻሕፍትን ጥቅም ተረድተው ለልጆቻቸው መጻሕፍትን በመግዛት ተነሳሽነትን ሊፈጥሩላቸው ይገባል ሲል ተናግሯል።

ለአብነትም፤ ቀደም ባለው ጊዜ የነበሩ ወላጆች ብዙ የህፃናት መጻሕፍት ባልነበሩበትና ወላጆችም ዘመናዊ ትምህርት ባልቀሰሙበት ወቅት በቃል በሚነገሩ ታሪኮች፣ ተረቶችና ሥነ-ቃሎች ልጆችን ሲያስተምሩ እንደነበር ያነሳል።

ይህ ደግሞ ማኅበረሰቡንና አገርን ለመገንባት ከፍተኛ መነሻ ሆኖ ማገልገሉን ጠቅሶ፤ ይህንን ከግምት በማስገባት አሁን ላይ ያሉ ወላጆችም ልጆቻቸው የንባብ ልምድ እንዲኖራቸው ተግተው መሥራት እንዳለባቸው ነው የተናገረው። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም