ቀጥታ፡

ተመራቂዎች ዕውቀትን ከመልካም ሥነ ምግባር ጋር አስተሳስረው ሀገራቸውን በቅንነት ማገልገል ይገባቸዋል- ለገሠ ቱሉ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2016(ኢዜአ)፦የከፍተኛ ትምህርት ምሩቃን በተማሩበት ሙያ የቀሰሙትን ዕውቀት ከመልካም ሥነ ምግባር ጋር አስተሳስረው ሀገራቸውን በቅንነት እንዲያገለግሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ ለገሠ ቱሉ(ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።

የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ትምህርት መስኮች በመደበኛ፣ በማታና በተከታታይ መርሐ ግብራት ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 688 ተማሪዎችን ዛሬ ያስመረቀ ሲሆን ከተመራቂዎቹ መካከል 812ቱ ሴቶች ናቸው።


 

የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሠ ቱሉ(ዶክተር)፣ ዕለቱ ምሩቃኑ ወደ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ የሚሸጋገሩበት ቀን ነው ብለዋል።

ምሩቃኑ በተማሩበት ሙያ ዘርፍ ማህበረሰባቸውንና ሀገራቸውን ለማገልገል ኅላፊነት የሚወስዱበት ዕለት እንደሆነም እንዲሁ።

ተመራቂዎች በቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት ከመልካም ሥነ- ምግባር ጋር አስተሳስረው ሀገራቸውን በቅንነት እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ብርሐነ መስቀል ጠና(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ጥራት ያለው ትምህርትን ተደራሽ በማድረግ ብቁ የሰው ኃይል የማፍራት ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

 

ለግቡ መሳካትም የሰው ኃይል እና የተቋማዊ መሰረተ ልማትን አቅም የመገንባት ተግባራትን እያከናወነ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ከተመራቂዎች መካከል የሳይኮሎጂ ትምህርት የማዕረግ ምሩቁ ሌዊ ሰንበቶ እና የኢኮኖሚክስ ትምህርት ተመራቂዋ ዲቦራ ግርማ፥ በተማሩበት ሙያ ያገኙትን ዕውቀት ወደስራ ተርጉመው ሀገራቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም