ተመራቂ ተማሪዎች በተቋማት ውስጥ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለማቃለል የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ተመራቂ ተማሪዎች በተቋማት ውስጥ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለማቃለል የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች በተቋማት ውስጥ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር በማቃለል የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የዩኒቨርስቲው የቦርድ ሰብሳቢ ተመስገን ቡርቃ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በቀንና በማታ ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 269 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።
የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ተመስገን ቡርቃ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ተመራቂ ተማሪዎች በተቋማት ውስጥ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለማቃለል የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ይህም ብቻ ሳይሆን ከአድሎና ከሙስና የፀዳ አገልግሎት በመስጠት የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት የተሳለጠ ለማድረግ አገሪቷ የምትጠብቅባቸውን ሙያዊ ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ነው የገለጹት።
በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያስመዘገበ ያለውን አንጸባራቂ ድሎች እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የተጀመረውን የለውጥ ሥራዎች ትግበራ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
ጎን ለጎንም ዩኒቨርሲቲው የምርምር ተቋም እንደመሆኑ መጠን ችግር ፈቺና ለፖሊሲ ግብዓትነት የሚውሉ የምርምር ሥራዎችን በማውጣት የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ እንዲያጠናክርም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ከጊዜ ወደ ጊዜ ተወዳዳሪና ተመራጭነቱ እያደገ በመምጣቱ ተቀብሎ የሚያስተምራቸው ተማሪዎች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል።
በጥናትና ምርምር ሥራዎችም በርካታ አመርቂ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም ለሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት መሳለጥ የሚያበረክተውን ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት የሚያከናውነውን ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።