ዩኒቨርሲቲው ሳይንስና በቴክኖሎጂ ዘርፍ የጀመራቸው የምርምር ስራዎች አገርን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያግዙ ናቸው -አለሙ ስሜ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው ሳይንስና በቴክኖሎጂ ዘርፍ የጀመራቸው የምርምር ስራዎች አገርን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያግዙ ናቸው -አለሙ ስሜ (ዶ/ር)

አዳማ ፤ ሰኔ 29/2016 (ኢዜአ)፡- የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዘርፍ የጀመራቸው የምርምር ስራዎች አገርን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያግዙ መሆናቸውን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 102 ተማሪዎች ዛሬ አስመረቋል።
በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፣ የአየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ እና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ፣ ዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ረገድ የጀመራቸውን የምርምር ስራዎች አገርን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያግዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ብቁ፣ ተወዳዳሪና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውን የሰው ሃይል ማፍራት የበለጠ መጠናከር እንዳለበትም አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው በምስራቅ አፍሪካ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከል ለመሆን ያስቀመጠውን ግብ እንዲሳካም ሁሉም ድጋፍና ትብብር ማድረግ እንዳለበት ነው የተናገሩት።
የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በሳይንስና ቴክኖሎጂ ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት ተማሪዎችን አወዳድሮ በመቀበል በተለያዩ የሙያ መስኮች እያሰለጠ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም የህዋ ሳይንስ ምርምር፣ የተለያዩ የኢንጂነሪንግ ዘርፎችን ጨምሮ ስምንት የልህቀት ማዕከላት በመክፈት የአገሪቷ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ስራዎች በምርምር ለመደገፍ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።