ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ተማሪዎች ዝግጅት። - ኢዜአ አማርኛ
ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ተማሪዎች ዝግጅት።

በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚተዳደረው የሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ሒሳብ የላቀ ዕውቀት ያላቸውን ተማሪዎች በመቀበል ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያስተምራል።
ትምህርት ቤቱ በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና በየዓመቱ አስፈትነው በተሻለ ውጤት ከሚያሳልፉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከልም አንዱ ሲሆን ዘንድሮ 61 ተማሪዎችን ያስፈትናል።
ኢዜአ ከቀናት በኋላ በወረቀት እና በበይነ-መረብ አማራጮች ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ቅድመ-ዝግጅት በተመለከተ ተፈታኝ ተማሪዎችን እና የአስተዳደር አባላትን አነጋግሯል።
ከተፈታኞች መካከል ናሆም መስፍን እና ሊያ ሰማኸኝ በዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ራሳቸውን በዕውቀትና ሥነ-ልቦና ማዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
ፈተናው ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርቶችን ያማከለ በመሆኑ የሚፈተኗቸውን ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች በመከለስ እና ከዚህ ቀደም የተሰጡ የፈተና ጥያቄዎችን በማመሳከር ጊዜ ሰጥተው ማጥናታቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ተማሪ ሴሩኪያስ ተዋህዶ እና ሶሊያና ተስፋ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚያስገባ አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ የሞዴል ፈተናዎችን በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ ራስን የማብቃት ጥረት ማድረጋቸውን ገልፀዋል።
ተፈታኞቹ እንደሚሉት ከራሳቸው በተጨማሪ በሌሎች ትምህርት ቤቶች የሚሰጡ ሞዴል ፈተናዎችን በጥሞና በመሥራት ለሀገር አቀፉ ፈተና በዕውቀት ብቻ ሳይሆን ሥነ-ልቦናዊ ዝግጅት ስለማድረጋቸው ነው የሚናገሩት።
የሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ዳይሬክተር ዘላለም ሲሳይ እንዳሉት፤ ትምህርት ቤቱ ለተፈታኞቹ ፕሮጀክቶችን እና ጠንካራ የሞዴል ፈተናዎችን ደጋግሞ በመፈተን ራሳቸውን እንዲያበቁ ጥረት አድርጓል።
የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር)፤ የሳይንስ ሼርድ ካምፓስ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በማስተማር ዩኒቨርሲቲው ሀገራዊ ኃላፊነቱን የሚወጣበት አንዱ መንገድ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይም የትምህርትን ጥራት ችግር ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት ብቃት እና ክህሎት እንዲላበሱ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
በዚህም የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ሼርድ ካምፓስን ማቋቋምን ጨምሮ ሀገር የሚረከብ ትውልድ ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።
የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ከሐምሌ 3 እስከ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ለሶሻል ሳይንስ እንዲሁም ከሐምሌ 9 እስከ 11 ደግሞ ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች እንደሚሰጥ ትምህርት ሚኒስቴር ማስታውቁ ይታወሳል።