የ2016 በጀት ዓመት የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ውጤታማ ተግባራት የተከናወነበት ነው - የምክር ቤቱ አባላት

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2016(ኢዜአ)፦ የ2016 በጀት ዓመት የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን በተቋማት ክትትል፣ ቁጥጥርና ሕጎችን በማፅደቅ በኩል ውጤታማ ተግባራት የተከናወነበት መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ገለፁ።

በበጀት ዓመቱ የሕዝብ ውክልናና የፓርላማ ዲፕሎማሲ ሥራ በአግባቡ መከናወናቸውንም ነው የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና አባላቱ የገለፁት።

በምክር ቤቱ የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ እንዳሉት፤ ቋሚ ኮሚቴው ምክር ቤቱ በሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሠረት በ2016 በጀት ዓመት በሥሩ ያሉ ተቋማትን የማስተባበርና የመከታተል ሥራ ሰርቷል።


 

ከምክር ቤት ወደ ቋሚ ኮሚቴው ሕጎች ሲመሩ ተገቢውን አግባብ ጠብቀው እንዲፀድቁ የማድረግ፣ አስፈጻሚውን የመከታተልና በቋሚ ኮሚቴው ሥር ያሉ ተቋማትን መከታተል ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ስድስት የከተማ መስክ ሥራዎችን ለመሥራት አቅዶ አምስት እንዲሁም ስድስት የገጠር መስክ ምልከታ ለማድረግ አቅዶ ሙሉ በሙሉ ማከናወን መቻሉንም አቶ ደሳለኝ ተናግረዋል።

ቋሚ ኮሚቴው የሚከታተላቸው የገንዘብ ሚኒስቴር፣ ገቢዎች ሚኒስቴር፣ ፕላንና ልማት ሚኒስቴር እንዲሁም ብሔራዊ ባንክ ከነተጠሪ ተቋማታቸው እንደሆኑ ገልፀዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በሥሩ ያሉ ተቋማትን አፈጻጸም በየጊዜው በመገምገም ግብረ-መልስ ሲሰጥ መቆየቱን አንስተው፤ በዚህ በኩል ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ጠቁመዋል። 

በበጀት ዓመቱ ከግብር ስወራና ደረሰኝ ማጭበርበር፣ ኮንትሮባንድ ንግድና የሚጓተቱ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ በማድረግ ያለውን ክፍተት ለመሙላት በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አሬሬ ሞሲሳ በበኩላቸው፤ የ2016 በጀት ዓመት እንደ ምክር ቤት ውጤቶች የተመዘገቡበት የሥራ ዘመን መሆኑን አመላክተዋል።


 

የሥራ ዘመኑ መራጩ ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄ ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት በማቅረብ ምላሽ እንዲያገኙ የተሰራበት መሆኑን የገለፁት ደግሞ የምክር ቤቱ አባል የሆኑት አቶ ከበደ ገነቴ እና ነጃት ግርማ(ዶ/ር) ናቸው። 


 

የተቋማቱን አፈጻጸም ከመገምገም ባለፈ የመስክ ሥራዎች በማከናወን በኩልም ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ገልፀዋል።


 

የምክር ቤቱ አባላት በቀጣይ ወደ መረጣቸው አካባቢ ሲሄዱ ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በማምጣት እንዲመለሱ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም