በቡና አቅርቦትና አላላክ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በቅንጅት ይሰራል--የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር - ኢዜአ አማርኛ
በቡና አቅርቦትና አላላክ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በቅንጅት ይሰራል--የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር
ሀዋሳ ፤ ሰኔ 29/2016 (ኢዜአ)፡- በቡና ምርት አቅርቦትና አላላክ ላይ የሚስተዋሉ የጥራት ችግሮችን ለመፍታት ከአቅራቢዎች እና ላኪዎች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር አስታወቀ።
ቡና አቅራቢዎችና ላኪዎች በበኩላቸው ወደውጪ የሚለካውን የቡና ምርት ጥራትና መጠን በማሳደግ ገቢን ለማሳዳግ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በሀዋሳ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው የብሔራዊ ቡና ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ እንዳሉት፣ በቡና ንግድ የሚስተዋሉ የጥራት፣ የአቅርቦትና የግብይት ችግሮች ለስራው እንቅፋት ሆነው ቆይተዋል።
ቡና በሚዘጋጅበት ወቅት የምርት ጥራት መጓደልና አቅርቦት ማነስ ችግሮች ከቡና ምርት የሚፈለገው ያህል ገቢ እንዳይገኝ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።
ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን ጠቁመው፣ "በቡና ግብይት ምንም እሴት የማይጨምሩ ደላሎችን ከገበያው በማስወጣት ቡና አምራች፣ አቅራቢና ላኪው ከዘርፉ የሚያገኙትን ጥቅም ለማሳደግ በቅንጅት ይሰራል" ብለዋል።
ቀደም ሲል አቅራቢውና ላኪው የሚገናኙበት መድረክ ባለመኖሩ ግብይቱ በደላላ በኩል ሲፈጸም እንደነበር ያስታወሱት አቶ ዘሪሁን፣ ለቀጣይ አቅራቢ እና ላኪውን በቀጥታ የሚያገናኝ ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ጠቁመዋል።
"ይህም ችግሩን በመፍታት አቅራቢና ላኪ በቅንጅት የሚሰሩበት፣ በጋራ እየተገናኙ የሚመክሩበት እና ግዥውን በቀጥታ የሚያከናውኑበት እድል ይፈጥራል" ብለዋል።
ከእዚህ በተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ እና የቡና ጥራትን ለማምጣት እንደሚያስችል ነው የገለጹት።
በሲዳማ ክልል አቤላ ወረዳ የረመዳ የታጠበ ቡና አቅራቢ ድርጅት ባለቤት አቶ መርጊያ ተገኝ እንዳሉት የቡና ንግድ ላይ ከግብይትና ክፍያ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮች በምርት አቅርቦትና ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
አቅራቢው ከአምራቹ የተረከበውን ቡና ለላኪዎች ሲያቀርብ ወዲያው ካልተከፈለው ሌላ ምርት ለማቅረብ አቅም ያጥረዋል ብለዋል።
አቶ መርጊያ እንዳሉት ደላሎች በምርቱም ሆነ በአቅርቦቱ ምንም አይነት ሚና ሳይኖራቸው አቅራቢውና ላኪው መሀል በመግባት በቡና ንግዱ ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩ ይገኛሉ።
ችግሩን ለመፍታት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ቡና አቅራቢና ላኪውን የሚገናኙበት መድረክ ማዘጋጀቱ እና የቡና ማህበሩም ሁለቱን የሚያገናኝ ስርዓት ለመዘርጋት የጀመረው ሥራ በዘርፉ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
"የቡና ጥራትን፣ አቅርቦትና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ እንዲሁም በቡና ንግድ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት አምራች፣ አቅራቢ እና ላኪ በቅንጅት መስራታቸው ፋይዳው የጎላ ነው" ያሉት ደግሞ በቡና ላኪ ሥራ የተሰማሩት አቶ ዳንኤል ዘርያቆብ ናቸው።
“ላኪዎች ለተረከቡት ቡና ተገቢውን ዋጋ በፍጥነት ከመፈጸም አንጻር ክፍተቶች አሉ፤ ቀደ ምሲል ቡና በዱቤ ወስዶ ሳይከፈል የመቅረት ሁኔታ ነበር” ብለዋል።
ይህም በቡና ንግድ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሲያሳድር ቆይቷል ያሉት አቶ ዳንኤል፣ ችግሩ እንዲፈታ ግብይቱ ያለ ደላላ ጣልቃ ገብነት እንዲከናወን የሚያስችል የግብይት ስርዓት መዘርጋት ይገባል ብለዋል።
አቅራቢና ላኪ በአካል እንዲገናኙ የተፈጠረው መድረክ በችግሮች ላይ ተወያይቶ የቡና ምርትና ጥራትን የሚያሳድጉ ሥራዎችን በጋራ ለመስራት ስለሚያስችል በቀጣይም መጠናከር አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ቡና አምራች፣ አቅራቢ እና ላኪዎችን ያገናኘና በቡና አቅርቦት ጥራትና ምርት መጠን ዙሪያ የሚመክር አውደ ርዕይ እና የውይይት መድረክ በሀዋሳ ከተማ ማዘጋጀቱ የሚታወስ ነው።