ቀጥታ፡

በክልሉ የተተከሉ ችግኞች የአፈር ለምነትና የአየር ንብረት ለውጥን ከመጠበቅ አንጻር ውጤት እያስገኙ ነው - አቶ ጸጋዬ ማሞ

ሚዛን አማን፤ ሰኔ 29/2016(ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የተተከሉ ችግኞች የአፈር ለምነትና የአየር ንብረት ለውጥን ከመጠበቅ አንጻር ውጤት እያስገኙ መሆኑን የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ ገለጹ።

በክልሉ ቤንች ሸኮ ዞን የዘንድሮ የክረምት አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በይፋ ተጀምሯል።

 

የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ በዞኑ ሰሪትን ቀበሌ በመገኘት ተከላውን ያስጀመሩ ሲሆን ሌሎች የክልሉና የዞን የሥራ ኃላፊዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተከላው ተሳትፈዋል።

አቶ ጸጋዬ ማሞ በወቅቱ እንዳሉት ችግኝ መትከል ለትውልድ አረንጓዴና የአየር ንብረቱ የተጠበቀ አካባቢን ከማስረከብ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ ነው።

እንደ ክልል ባለፉት ዓመታት በርካታ የደንና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰው፣ በዚህም የአፈር ለምነትና የአየር ንብረት ለውጥን ከመጠበቅ አንጻር አዎንታዊ ውጤት እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።

የባህር ዛፍ ተክል የመሬት ለምነትን ስለሚያጠፋ በሙዝ፣ በአቮካዶና መሰል ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በሚያስገኙ ችግኞች የመተካት ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አቶ ጸጋዬ ገልጸዋል።

ዛሬ ችግኝ የተተከለበት የሰሜን ቤንች ወረዳ በባህር ዛፍ ደን የተሸፈነ መሆኑን ጠቅሰው፣ ባህርዛፉን በፍራፍሬ በመተካት አካባቢውን የፍራፍሬ ክላስተር የማድረግና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን በበኩላቸው “በዞኑ ለግብርና ልማት መዋል ያለበት በርካታ ሄክታር መሬት በባህር ዛፍ በመሸፈኑ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሥራ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል” ብለዋል።


 

ይህንን ችግር ለመፍታት ቀደም ሲል በተሰሩ ሥራዎች በባህር ዛፍ ማሳ ላይ የተተከሉ የፍራፍሬ ምርቶች በአሁኑ ወቅት ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ለዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መዘጋጀቱን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ግብርና፣ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ጉብላ ናቸው። 

 

የተሻሻሉ ምርጥ የፍራፍሬ ችግኞች ተለይተው መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው "በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለአርሶ አደሩ አስተማማኝ የገቢ ምንጭ ይሆናሉ" ብለዋል።

በዛሬው የችግኝ ተከላ መርሀግብር ላይ የተሳተፉት የሰሪትን ቀበሌ አርሶ አደር ድጉ ባንካ አካባቢያቸው ዳገታማ በመሆኑና ለእርሻ ሥራ ምቹ ባለመሆኑ የፍራፍሬ ችግኝ እየተከሉ መሆኑን ገልጸዋል። 

"ዛሬ የምንተክለው ችግኝ የነገ ምግባችን እና የአካባቢ አየር ለውጥ ተጽኖን እንድንቋቋም ስለሚያስችለን ጠንክረን እንሠራለን" ሲሉ አረጋግጠዋል።

የአረንጓዴ ልማት ስራው በአካባቢያቸው ለውጥ እያመጣ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የአካባቢው አርሶ አደር አዲሱ ጴጥሮስ ናቸው።

ባለፉት ጊዜያት በተተከሉ ችግኞች የታየው ለውጥ ዘንድሮም ችግኝ ለመትከል እንዳነሳሳቸው ገልጸው፣ በተያዘው ክርምት በግልና በጋራ ችግኝ የመትከል ስራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም