የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ 1 ሺህ 688 ተማሪዎችን አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ 1 ሺህ 688 ተማሪዎችን አስመረቀ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2016(ኢዜአ)፦ የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 1 ሺህ 688 ተማሪዎችን አስመረቀ።
በተማሪዎች ምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እና የዩንቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)፣ የተመራቂ ተማሪዎች ቤተሰብና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የዛሬ ተመራቂዎች በመደበኛ፣ በማታ እና በተከታታይ መርሃ-ግብር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ መሆናቸውን በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ ተጠቁሟል።
የመንግሥት ኮሙኑኬሽን አገልግሎት ሚኒስትርና የዩንቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ምሩቃን ተማሪዎች ወደ አዲስ የህይወት ምዕራፍ መሸጋገር የሚያስችላቸውን የእውቀትና ክህሎት ልምድ በማካበት በመመረቃቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው ማኅበረሰብን ብሎም ሀገርን ወደ ተሻለች የእድገት ጎዳና እንድትጓዝ የማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
መንግሥት ትኩረት አድርጎ ከሚሰራባቸው አንኳር አጀንዳዎች ውስጥ አንዱ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ብቃት ያለው ዜጋ ማፍራት መሆኑን ገልፀዋል።
ለዚህም እውን መሆን መንግስት የትምህርት ሥርዓት ማሻሻል የሚቻልበት ተግባር ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ብርሀነመስቀል ጠና(ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መርሃ-ግብሮች ሲያስተምራቸው የነበሩ 1 ሺህ 688 ተማሪዎችን በዛሬው እለት አስመርቋል ብለዋል።
ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል 876 ወንዶች ሲሆኑ፤ 812ቱ ደግሞ ሴት ተማሪዎች ናቸው ሲሉም አክለዋል።
እንደ ሀገር የትምህርት ዘርፉን እየፈተነ ያለውን የትምህርት የጥራት ችግር ለመቅረፍ ዩኒቨርሲቲው ብቁ የሆነ የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት የጀመረውን ሥራ ከምንጊዜውም በላይ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።