መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በሰጠው ትኩረት የብድር አቅርቦቱ በእጥፍ ጨምሯል - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በሰጠው ትኩረት የብድር አቅርቦቱ በእጥፍ ጨምሯል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2016(ኢዜአ)፦ መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በሰጠው ትኩረት በዘንድሮው በጀት ዓመት የብድር አቅርቦቱ በእጥፍ ማሳደግ መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ተናገሩ።
ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የተሰጠው ትኩረት ለዘርፉ እመርታ የማይተካ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።
የዘርፉን እድገት ለማስቀጠል ቅንጅታዊ አሠራርን ከማጎልበት ባሻገር የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ማሻሻያን ጨምሮ በዘርፉ የሕግና አሠራር ማሻሻያዎች መደረጉን ገልፀዋል።
የአገሪቷን የተዛባ የውጭ የንግድ ሚዛን ለማሻሻል የተኪ ምርት ስትራቴጂ ተቀርፆ ወደ ሥራ በመገባቱ ከውጭ ሲገቡ የነበሩ 96 ምርቶች በአገር ውስጥ መተካታቸውን ጠቁመዋል።
በፋይናንስ አቅርቦት ረገድ ባለፉት አሥር ወራት ለከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ብቻ 42 ቢሊየን ብር ብድር መቅረቡንም ገልጸዋል።
ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ደግሞ 5 ቢሊየን ብር ብድር መሰጠቱንም እንዲሁ።
የብድር አቅርቦቱ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ማደጉን ገልጸው፤ ይህም መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
በአምራች ዘርፉ አዳዲስ ኢንቨስትመንት በመሳብ የአገር ውስጥ ምርት ድርሻን 10 በመቶ ማሳደግ እንደተቻለ አንስተው፤ በስትራቴጂክ ምርቶች ብቻ ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት ተችሏል ብለዋል።
ከአሠራር ማሻሻዎች መካከል የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት፣ የኃይል አቅርቦትና በመሠረተ-ልማት አቅርቦት ዙሪያ መጠነ-ሰፊ ማሻሻያዎች ስለመደረጋቸው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢንዱስትሪ ምርት ፍላጎት ያላት ሀገር በመሆኗ በዘርፉ ያለውን ኢንቨስትመንትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ለማሳደግ ቀጣይነት ያለው ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል።
የአገር ውስጥ ምርቶች ጥራት በተመለከተም በማኅበረሰቡ ዘንድ የተዛቡ ዕይታዎች እንዳሉ ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ምርት በሌሎች አገራት ገበያ ያለምንም ችግር እየተሸጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የአገር ውስጥ ምርቶች የራሳቸው የጥራት ደረጃ ወጥቶላቸው ተመርተው ወደ ገበያ እንደሚወጡም አስረድተዋል።
ሚኒስቴሩ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ከፋብሪካ ምርት ሂደታቸው ጀምሮ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ ክፍተቶች ሲገኙ እርምጃ እንደሚወስድም አረጋግጠዋል።