የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማን ያነሳል?  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወይስ መቻል?

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ሳምንት መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ መድን፣ መቻል ከድሬዳዋ ከተማ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።

ፕሪሚየር ሊጉ ዛሬ የሚጠናቀቅ ሲሆን በ30ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የዋንጫውን አሸናፊ የሚወስኑ ሁለት ተጠባቂ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ መድን ከቀኑ 10 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።


 

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች 3 ጊዜ ሲያሸንፍ 2 ጊዜ አቻ ወጥቷል። 

በ5ቱ ጨዋታዎች 11 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 3 ግቦችን አስተናግዷል።

በአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ61 ነጥብ በሊጉ ቀዳሚ ስፍራ ይገኛል።

ኢትዮጵያ መድን ካለፉት 5 ጨዋታዎች 4 ጊዜ ሲያሸንፍ 1 ጊዜ ተሸንፏል። በነዚህ 5 ጨዋታዎች 13 ግቦችን ሲያስቆጥር 3 ግቦች ተቆጥረውበታል።

በገብረመድህን ኃይሌ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ መድን በ40 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሁለቱ ክለቦች በሊጉ በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 4 ለ 1 ማሸነፉ ይታወሳል።

በሌላኛው የ30ኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሐ ግብር የዋንጫ ተፎካካሪው መቻል ከድሬዳዋ ከተማ በተመሳሳይ ከቀኑ 10 ሰዓት በሃዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ጨዋታውን ያደርጋል።

መቻል በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ጨዋታዎች 4 ጊዜ ሲያሸንፍ 1 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። 


በ5ቱ ጨዋታዎች 13 ጎሎችን ሲያስቆጥር 5 ግቦችን አስተናግዷል።

በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚመራው መቻል በ60 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ድሬዳዋ ከተማ ባለፉት 5 የሊጉ መርሐ ግብሮች 2 ጊዜ ሲያሸንፍ 3 ጊዜ ተሸንፏል። በነዚህ 5 ጨዋታዎች 5 ግቦችን ሲያገባ 10 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

በኮማንደር ሽመልስ አበበ የሚሰለጥነው ድሬዳዋ ከተማ በ40 ነጥብ ተመሳሳይ ነጥብ ባላቸው ኢትዮጵያ መድንና ሲዳማ ቡና በግብ ክፍያ ተበልጦ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት የሊጉ ጨዋታ መቻል 3 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዛሬው ጨዋታ ካሸነፈ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን ያነሳል። 

ንግድ ባንክ ተሸንፎ ወይ አቻ ወጥቶ በአንጻሩ መቻል ቢሸነፍ ወይም ነጥብ ቢጥል ንግድ ባንክ የዋንጫው ባለቤት ይሆናል።

መቻል ዋንጫውን ለማንሳት ማሸነፍና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሸነፍ ወይም አቻ መውጣት አለበት።

80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ የሚገኘው መቻል አሸናፊ ከሆነ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ1990 ዓ.ም ከጀመረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን ያነሳል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 28 እንዲሁም መቻል 19 የግብ ክፍያ አላቸው።

በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ የ30ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ጨዋታዎች ሻሸመኔ ከተማ ሀምበሪቾን 3 ለ 1 እንዲሁም ወልቂጤ ከተማ አዳማ ከተማን 1 ለ 0 አሸንፈዋል።

መስከረም 20 ቀን 2016 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ፍጻሜውን ያገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም