ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ - ደቡብ ሱዳን የጋራ ድንበር አስተዳዳሪዎች ስብሰባ የሁለቱን አገራት ትብብር ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችል ነው 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2016 (ኢዜአ)፡-  የኢትዮጵያ - ደቡብ ሱዳን የጋራ ድንበር አስተዳዳሪዎች ስብሰባ የሁለቱን አገራት ትብብር ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችል መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ፡፡

ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ - ደቡብ ሱዳን የጋራ ድንበር አስተዳዳሪዎች ስብሰባ ተጠናቋል።

የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች አገራቱ የጋራ ድንበር አስተዳደር ስብሰባ ማካሄዳቸውን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም የሁለቱ አገራት የህዝብ ለህዝብ፣ የንግድ ግንኙነት እንዲሁም ሰላምና ደህንነትን በጋራ የማስጠበቅ ተግባራቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በመግለጫው  ስብሰባው በሁለቱ አገራት መካከል የጋራ ድንበር ልማትን ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

በአገራቱ  መካከል የመሠረተ ልማት ትስስርንና የጋራ ድህንነትን ለማጠናከር እንዲሁ አይነተኛ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት፡፡

ሁለቱ አገራት በስብሰባው ድንበር ተሻጋሪ ደህንነትን እና የጋራ ልማትን ለማጎልበትም መግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

የዛሬው ሰብሰባም የጋራ ልማት፣ ተጠቃሚነትን፣ ሰላምን ከማረጋገጥ አንጻርም ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ማንዴ ሴማይ ኩምባ፣ ሁለቱ አገራት በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ተወያይተው መግባባት ላይ መድረሳቸው ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል፡፡ 


 

ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር እያደረገች ያለችው የሁለትዮሽ ግንኙነት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚፈጥርና የቀደመውን ሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በስብሳበው መግባባት ላይ የተደረሱባቸውን ጉዳዮች በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ደቡብ ሱዳን ቁርጠኛ መሆኗንም ጠቁመዋል፡፡  

በስብሰባውም የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡመድ ኡጁሉ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)፣ የደቡብ ሱዳን የክልል አስተዳዳሪዎችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም