ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ፕሮጀክቶችን በማሳካት ቃላችንን በተግባር እያሳየን እንገኛለን -አቶ ሽመልስ አብዲሳ - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ፕሮጀክቶችን በማሳካት ቃላችንን በተግባር እያሳየን እንገኛለን -አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2016 (ኢዜአ)፡- ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት፣ በጥራትና በብዛት በማሳካት ቃላችንን በተግባር እያሳየን እንገኛለን ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕስ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
መንግሥት የአሥር ዓመቱን የብልጽግና ጉዞ ዕቅድ ካወጣ በኋላ ሙሉ በሙሉ ከቀየራቸው አካሄዶች አንዱ የሕዝብ ቅሬታ ምንጭ ሆነው የሰነበቱና በፕሮጀክቶች ግንባታ ሂደትና አፈጻጸም ላይ የሚስተዋሉ ከፍተኛ ችግሮችን መቅረፍ እንደነበር አስታውሰዋል።
በዚህም ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት፣ በጥራትና በብዛት በማሳካት ቃላችንን በተግባር እያሳየን እንገኛለን ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ መሠረተ ልማት፣ የጤና አገልግሎት፣ ትምህርትና ቴክኖሎጂን በማስፋት ለአገር እድገትና ብልጽግና ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል ሲሉም ነው የገለጹት።
ዘንድሮም፤ ካለፉት ሦስት ዓመታት የቀሰምናቸውን ልምዶች፣ ከአመቱ የቁጭት ዕቅድን ጋር በማዳበል ከፕሮጀክቶች ግንባታ ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እየፈታን እንገኛለን ያሉት አቶ ሽመልስ፤ በተያዘላቸው በጀት፣ ጊዜ እና የጥራት ደረጃ በማጠናቀቅ የሕዝብ እርካታን ለማሳደግ እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።
በተጨማሪም፤ የፕሮጀክቶች ክትትልና አያያዝን በየጊዜው በከፍተኛ አመራር ደረጃ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ቆይተናል ሲሉም ገልጸዋል።
በዚህ የተነሳ፤ ከፕሮጀክቶቹ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ችግሮች፤ ማለትም የገበያ ግሽበት፣ የምርምርና ዲዛይን፣ የግንባታ ግብአቶች አቅርቦት እና ከተቋራጮች ጋር የተያያዙ ችግሮችን ሳይውሉ ሳያድሩ መፍትሄ መስጠት ችለናል ብለዋል።
በአጠቃላይ የተለመዱ የፕሮጀክቶች ግንባታ ሂደት የጋራ ችግሮች ይበልጥ እንዲቀንሱ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በተከታታይ 11,001፣ 20,070 እና 19,912 ፕሮጀክቶችን መጠናቀቃቸውን የገለጹት ርዕስ መስተዳድሩ፤ በአጠቃላይ 50,983 ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ ችለናል ሲሉ ጠቅሰዋል።
በ2016 በጀት ዓመት በ 110 ነጥብ 91 ቢሊየን ብር እየተተገበሩ ካሉት 31,167 ፕሮጀክቶች ውስጥ 30,261 ፕሮጀክቶች (97%) እንደ ክልል በእንቅስቃሴ ውስጥ ናቸውም ብለዋል።
ከእነዚህ ውስጥ በ79 ነጥብ 43 ቢሊዮን ብር ወጪ 20,664 ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ዘንድሮ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህም ካለፉት ሦስት ዓመታት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሻሻል የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በዚህ የበጀት ዓመት ለምረቃ ከተዘጋጁት ውስጥ 7,636 የሚሆኑ ፕሮጀክቶች በ61 ነጥብ 58 ቢሊዮን ብር በመንግስት በጀት፣ 13,028 ፕሮጀክቶች በ17 ነጥብ 85 ቢሊዮን ብር በዜግነት አገልግሎት መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
ዘንድሮ በዜግነት አገልጎት ዘርፍ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ የተደረገው እንቅስቃሴ ካለፉት ሶስት አመታት ጋር ሲነጻጸር የላቀ መሆኑ ጠቅሰዋል።
በዚህም በትምህርት ዘርፍ የቡኡራ ቦሩ ትምህርት ቤቶችና ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ፣ በጤናው ዘርፍ፣ የአዳዲስ ጤና ኬላዎች፣ ተጨማሪ የጤና ተቋማት፣ የማህበረሰብ ሞዴል ፋርማሲ እና በርካታ የእናቶች ማቆያዎች ግንባታ በዜግነት አገልጎት ተከናውነዋል።
ከውሃ አንፃር የምንጭ ማጎልበት፣ የቤተሰብ እና የማህበረሰብ ደረጃ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ እና የመጠጥ ውሃ መስመር ዝርጋታ ተከናውነዋል ብልዋል።
መንገዶችን በተመለከተ የአዳዲስ የቀበሌ ለቀበሌ አገናኝ የጠጠር መንገዶች ግንባታና ጥገና፣ ትንንሽ ድልድይ ግንባታ፣ የውስጥ ለውስጥ አዳዲስ መንገዶች ግንባታ፣ ጥርብ ድንጋይ መንገዶች ዝርጋታ መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የጎርፍ ማፋሰሻ ዲች ግንባታ፣ የጥቃቅን እና አነስተኛ ሼዶች ግንባታ፣ የገበያ ማዕከላት ግንባታ፣ የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት ግንባታ፣ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች ግንባታ፣ የቀበሌ ጽሕፈት ቤቶች ግንባታ፣ ወዘተ በህዝባችን የዜግነት አገልግሎት መሰራት ተችሏል ብለዋል።
በአጠቃላይ ፕሮጀክቶቻችን በተያዘላቸው ጊዜ፤ በጀትና ጥራት ማጠናቀቅ ተጨማሪ ወጪዎች በመቀነስ የህዝባችንን ህይወት በማሻሻል የክልላችንን፤ እንዲሁም የአገራችንን ኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ አዎንታዊ መሻሻልን የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰዋል።
እነዚህ አመላካቾች መንግስት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ያሳየውን ውጤታማ እቅድ፤ ተአማኝነት እና ወደፊት ዕቅዶቹን ሳያዛንፍ ለመፈጸም ያለውን ቁርጠኝነት የሚያንፀባርቁ መሆናቸውንና ለእስካሁኑ ስኬት ህዝባችን ለተወጣው ከፍተኛ ኃላፊነት ያለኝን ታላቅ አክብሮት እገልጻለሁ ብለዋል፡፡