ቀጥታ፡

ወጣቶች በጎ ተግባራት ላይ የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል-ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)

አርባ ምንጭ፤ ሰኔ 28/2016 (ኢዜአ)፦ ወጣቶች በጎነትና አብሮነት ላይ በማተኮር የኢትዮጵያ ከፍታ እንዲረጋገጥ የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ገለጹ።

"በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ 3ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የወሰን ተሻጋሪ ወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዛሬ በአርባምንጭ ከተማ በይፋ ተጀምሯል።


 

በመድረኩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)፣ ወጣቶች በጎነትና አብሮነት ላይ በማተኮር የኢትዮጵያ ከፍታ እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ህብረ ብሔራዊ አንድነትንና አብሮነት የሚያጎለብትና ኢትዮጵያ የጀመረችው የብልጽግና ጉዞ እንዲሳካ ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም በመሆኑ "በዚሁ በጎ ተግባር ላይ ለሚሳተፉ ወጣቶች ምስጋና አለኝ" ብለዋል ሚኒስትሯ።

በዚህ ክረምት ወጣቶቹ የሚተገብሩት 14 የበጎ ፍቃድ ሥራ ዘርፎች የተለዩ መሆናቸውን ጠቅሰው ከነዚህ መካከልም የማህበረሰብ ሰላምና ደህንነት፣ የግብርና ልማት፣ የሌማት ትሩፋት፣ የትምህርትና ስልጠና እንዲሁም የጤና አገልግሎትን ጠቅሰዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ማርቆስ ማቲዎስ በበኩላቸው የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች አንድነትና አብሮነትን ከማጠናከር አንጻር ጉልህ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።


 

በክልሉም በዘንድሮ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ሶስት ሺህ የአቅም ደካማ ቤቶችን ለመገንባት መታቀዱን ተናግረዋል።

ከወሰን ተሻጋሪ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች መካከል ከጋምቤላ ክልል የመጣው ወጣት ተስላዋት ቶንግ፣ በጎ ተግባር የህሊና እርካታን የሚሰጥ ነው ይላል።

በወሰን ተሻጋሪ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራው ህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ አንድነትን የሚያጎለብት በመሆኑ በአገልግሎቱ የነቃ ተሳትፎ እንደሚያደርግ ገልጿል።

ከኦሮሚያ ክልል የመጣው ወጣት ሙባረክ ሰይፈድን፣ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ተናግሯል።

ይህም በመሆኑ በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ደስተኛ ሆኖ እየተሳተፈ መሆኑን ገልጿል።

በዚሁ መርሃ ግብር የሚኒስቴሩና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ ወጣቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም