ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለኮከብ እጩ ተጫዋቾች ተመልካቾች እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድምጽ መስጠት ይችላሉ - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለኮከብ እጩ ተጫዋቾች ተመልካቾች እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድምጽ መስጠት ይችላሉ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2016(ኢዜአ)፦ለ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የኮከብ ተጫዋች እጩዎች የተመልካቾች ድምጽ አሰጣጥ እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ እንደሚቆይ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር አስታወቀ።
አክሲዮን ማህበሩ የ2016 የሊጉን ኮከብ ተጫዋች እጩዎች ዝርዝር ሰኔ 19 ቀን 2016 ዓ.ም ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን ተመልካቾች ለተጫዋቾች ድምጽ መስጠት የሚችሉበት አማራጭ መዘጋጀቱም ይታወቃል።
ሰኔ 19 ቀን 2016 ዓ.ም የተጀመረው የተመልካቾች ድምጽ የመስጠት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ እንደሚቆይ ኢዜአ ከማህበሩ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ተመልካቾች በተለያየ ዘርፍ የቀረቡትን ተጫዋቾች በ https://t.me/ethiopianlea/17849 በአክሲዮን ማህበሩ የቴሌግራም ገጽ ድምጽ መስጠት እንደሚችሉ ጠቁሟል።
አክሲዮን ማህበሩ ለኮከብ ተጫዋችነት ሽልማት 7 እጩ ተጫዋቾችን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
እነዚህም የመቻል የአማካይ ተጫዋቾች ሽመልስ በቀለና ከነዓን ማርክነህ ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምበል ፈቱዲን ጀማልና ጋናዊው የክለቡ አማካይ ተጨዋች ባሲሩ ዑመር ፣ የባህር ዳር ከተማው የክንፍ መስመር ተጫዋች ቸርነት ጉግሳ፣ የወላይታ ድቻ አጥቂ ቢንያም ፍቅሬና ኤርትራዊው የሃዋሳ ከተማ የፊት መስመር ተሰላፊ አሊ ሱሌማን በእጩነት የቀረቡ ናቸው ።
በዚሁ መሰረት ፍሬው ጌታሁን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አቡበከር ኑራ ከኢትዮጵያ መድንና ሰዒድ ሀብታሙ ከአዳማ ከተማ የኮከብ ግብ ጠባቂ እጩዎች ናቸው።
በኮከብ ወጣት ተስፈኛ ተጨዋች ዘርፍ ወገኔ ገዛኸኝ ከኢትዮጵያ መድን፣ ተመስገን ብርሃኑ ከሀድያ ሆሳዕና፣ ዮሐንስ መንግስቱ ከመቻል፣በፍቃዱ አለማየሁ ከኢትዮጵያ ቡና፣ መድን ተክሉ ከወልቂጤ ከተማና ቢኒያም አይተን ከአዳማ ከተማ እጩዎች ዝርዝር ውስጥ ገብተዋል።
አክሲዮን ማህበሩ በኮከብ ወጣት ተስፈኛ ተጨዋች ዘርፍ በመጀመሪያ ይፋ ያደረገ አምስት ተጫዋቾችን ነበር።
ይሁንና የእጩዎች ዝርዝር ከተለቀቀ በኋላ ከአዳማ ስፖርት ክለብ በደብዳቤ በመጣ መረጃና ጥያቄ መሰረት ተጫዋች ቢንያም አይተን ከተመዘገቡ አስር የቢጫ ወይም የልዩ ቴሴራ ከ23 ዓመት በታች አንዱ መሆኑን ማህበሩ በማረጋገጡ በእጩነት እንዲካተት ተደርጓል።
ከተመልካቾች ድምጽ በተጨማሪ አሰልጣኞች፣ ጋዜጠኞችና የሊጉን ጨዋታ የቀጥታ ስርጭት መብት የወሰደው የደቡብ አፍሪካው ሱፐር ስፖርት የቴሌቪዥን ጣቢያ በድምጽ አሰጣጡ ድርሻ እንዳላቸው ማህበሩ ገልጿል።
የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የኮከብ ተጫዋቾች የሽልማት ስነ- ስርዓት የሚካሄድበት ጊዜ በቀጣይ ይፋ እንደሚደረግም አመልክቷል።