ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ተግባራት ይጠናከራሉ - ዶክተር ሙሉነሽ ደሴ

ባህር ዳር ፤ ሰኔ 28/2016 (ኢዜአ)፦  በአማራ ክልል  የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ተግባራት ይጠናከራሉ ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማእረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሙሉነሽ ደሴ ገለጹ።

በክልሉ የወባ በሽታ ስርጭትን መከላከል ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ በባህር ዳር ተካሂዷል።

ዶክተር ሙሉነሽ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ በየወቅቱ የሚከሰተውን የወባ በሽታ በመከላከል አምራች ዜጋ መፍጠር  ይገባል።

በዚህም በክልሉ ከበልግ የዝናብ ወቅት ጀምሮ የተከሰተውንና በክረምቱ ሊቀጥል የሚችለውን የወባ በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶ እየተሰራበት ነው ብለዋል።

በዚህም የአጎበር አጠቃቀምን በማሻሻል፣ ለወባ መራቢያ ምቹ የሆኑ አካባቢዎች ያለውን ውሃ በማፋሰስና በማዳረቅ እንዲሁም የኬሚካል ርጭት በማካሄድ ለመከላከል ትኩረት መደረጉን አስረድተዋል።

የጤና ሚኒስቴርና ባለድርሻ አካላት የወባ በሽታን ለመከላከል የላቦራቶርና ሌሎች የህክምና መሣሪያዎች፣ የኬሚካልና ሌሎች ግብዓቶች በማሟላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ዶክተር ሙሉነሽ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው እንደ ሀገር የተከሰተውን የወባ ስርጭት ለመቀልበስ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

ተቋማቸውና ጤና ሚኒስቴር የከፋ የወባ ስርጭት ባለባቸው 222 ወረዳዎች በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸው፤ በወረዳዎቹ ያለውን የወባ ስርጭት ወደ 50 በመቶ ለማውረድ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከነዚህ ወረዳዎች ውስጥም 34ቱ የሚገኙት በአማራ ክልል መሆኑንና  በሽታውን ለመቆጣጠር የቅኝት ሥራን ማጠናከር፣ ኬሚካል በመርጨትና አዳዲስ አጎበሮች በማሰራጨት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ  አቶ ገስጥ ጥላሁን እንደገለጹት የዛሬው መድረክ አላማ ለባለድርሻ አካላት በቂ ግንዛቤ በመፍጠር በሽታውን ለመከላከልና ለማከም ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ ነው።

በክልሉ በበጀት ዓመቱ በወባ በሽታ የተያዙ ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገቢው ምርመራና ህክምና ተሰጥቷቸው መዳናቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት እየጨመረ የመጣውን የወባ ስርጭት ለመቀነስ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የአካባቢ ክትትልና ቁጥጥር ስራና ህክምና እየተሰጠ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ ናቸው።

በመድረኩ የፌዴራል፣ የክልሉና የዞን እንዲሁም የወረዳ የዘርፉ አመራር አባላትና ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም