ቀጥታ፡

ከብሔራዊ የኃይል ቋት ርቀው የሚገኙ አካባቢዎች ከፀኃይ ኃይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እየሆኑ ነው

ደሎ መና፤ ሰኔ 28/2016 (ኢዜአ)፦ከብሔራዊ የኃይል ቋት ርቀው የሚገኙ አካባቢዎች ከፀኃይ ኃይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመደረግ ላይ  መሆኑን  የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር  ገለጸ። 

የፊዴራልና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ  የስራ ኃላፊዎች በምሥራቅ ቦረና ዞን ምዕራብ ወላቡ ወረዳ ከ110 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ በጀት የተገነቡ በፀሐይ ኃይል (ሶላር) የሚሰሩ የመብራት ፕሮጀክቶችን መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል። 


 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ(ዶ/ር) በምረቃው ወቅት፤ ከአገሪቱ የመልከዓ ምድር አቀማመጥና የተበታተነ አሰፋፈር የተነሳ ሁሉንም ህዝብ ከብሔራዊ ቋት የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ አስቸጋሪ ነው ብለዋል። 

መንግስት ከብሔራዊ የኃይል ቋት ርቀው የሚገኙ አካባቢዎች ከተለያዩ ታዳሽ የኃይል አማራጮች በተለይ ከፀኃይ ሃይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል። 

በምዕራብ ወላቡ ወረዳ 'ሆቦርሶ' ቀበሌ ተገንብተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩት ከፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጩ ፕሮጀክቶች የዚሁ ጥረት ማሳያ ናቸው። 

ፕሮጀክቶቹ 270 ኪሎ ዋት ሀይል የማመንጨት አቅም ያላቸው በመሆኑ ለመኖሪያ ቤቶች፣ ለማምረቻ ተቋማት፣ ለጤና፣ ለትምህርትና ለመንግስታዊ ተቋማት በቂ ኃይል ማቅረብ እንደሚችሉ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል። 

ከመንግሥት በተመደበና ከአጋር አካላት በተገኘ 110 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡት እነዚሁ ሁለት ፕሮጀክቶች መሥመር ተዘርግቶላቸው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አስታውቀዋል። 

ፕሮጀክቶቹ ከ3ሺህ ለሚበልጡ አባወራዎች  ለ25 ዓመታት የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል። 

በገጠሩ አካባቢ ለሚከናወኑ የመስኖ ልማት ሥራን በማሳለጥ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዙ ተናግረዋል። 

የአካባቢውን ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ከማድረጋቸው ባሻገር በማህበራት ለተደራጁ ከ400 ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረጋቸውን አመልክተዋል። 

የኦሮሚያ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ከድር ሁሴን በበኩላቸው፤ የክልሉ መንግስት በተለይ የአርብቶ አደሩ ኑሮ እንዲቀየርና ተጠቃሚነቱ ይበልጥ እንዲረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል። 


በተለይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ አካባቢ ተደራሽ መሆናቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ  ተጠቃሚነቱ ይበልጥ እንዲረጋገጥ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት። 

የአካባቢው ነዋሪ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ባለመሆኑ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተግዳሮቶች ተጋልጦ መቆየቱን የተናገሩት  የምዕራብ ወላቡ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን ኡመር ናቸው። 


 

በአሁኑ ወቅት መንግስት የአካባቢውን የልማት እምቅ አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት ለአገልግሎት ያበቃው በፀኃይ ኃይል የሚሰራው ፕሮጀክት በዘርፉ ሲያጋጥሙ የነበሩ ተግዳሮቶች እንዲቀርፉ ያደርጋል ነው ያሉት። 

የሆቦርሶ ቀበሌ ነዋሪው ሐጅ ሁሴን ሶሞ በሰጡት አስተያየት፤ ፕሮጀክቶቹ የቀበሌያቸው ነዋሪዎችን ከጨለማ በማውጣት ብርሃን እንዲያዩ ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል። 


 

የሶላር ሀይል ፕሮጀክቶቹ ረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ጥበቃና እንክብካቤ እንደሚያደርግላቸው የተናገሩት ደግሞ ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አቶ አደም አብደላ ናቸው። 

የሶላር አነስተኛ የሀይል ጣቢያዎቹ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኦሮሚያ ውኃና ኢነርጂ ቢሮና ጂ.አይ.ዜድ ጋር በመተባበር የተሰሩ መሆናቸው በምረቃው ወቅት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም