የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ይበልጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትጋት እየሰራ ነው - አቶ መስፍን ጣሰው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ይበልጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትጋት እየሰራ ነው - አቶ መስፍን ጣሰው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ይበልጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትጋት እየሰራ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
አየር መንገዱ በቅርቡ ከስካይ ትራክስ ዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅት የ2024 ምርጡ የአፍሪካ አየር መንገድ ሽልማት መውሰዱ ይታወሳል።
አየር መንገዱ ይህንን ሽልማት ለተከታታይ ሰባት ዓመታት ማሸነፉም ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ፣ የደንበኞችን ፍላጎት በመከተል አገልግሎቱን ለማላቅ በየጊዜው አዳዲስ አሰራሮችን እንደሚከተል ገልጸዋል።
በዚህም ስካይ ትራክስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞችን በቃለ መጠይቅና በተለያዩ መንገዶች ዳሰሳ በማድረግ ለ7 ተከታታይ አመታት የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ አድርጎ መሸለሙን ገልጸዋል።
በቀጣይም አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማስቀጠል በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በሌላ በኩል አየር መንገዱ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትን አየር መንገድ ለማቋቋም እየተነጋገረ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም፣ ከእስዋቲኒ መንግስት ጋር ብሔራዊ አየር መንገዳቸውን ለማቋቋም በቅርቡ መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
አየር መንገዱ የራሱን የአዋጭነት ጥናት በማድረግ ከበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የሚመጡትን ጥያቄዎች ለመመለስ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
አየር መንገዱ በቶጎ፣ማላዊና ዛምቢያ አየር መንገዶች ውስጥ ባለው ድርሻም ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሉት 147 አውሮፕላኖች 136 በላይ ዓለም አቀፍና 22 የአገር ውስጥ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል።