የአከራይና ተከራይ ውል የሁለቱም ወገኖች መብትና መልካም ግንኙነት እንዲጠናከር የሚያደርግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአከራይና ተከራይ ውል የሁለቱም ወገኖች መብትና መልካም ግንኙነት እንዲጠናከር የሚያደርግ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2016(ኢዜአ)፦ የአከራይና ተከራይ ግንኙነት ወደ ሕጋዊ አሰራር እንዲገባ መደረጉ የሁለቱም ወገኖች መብት እንዲጠበቅና መልካም ግንኙነት እንዲጠናከር የሚያደረግ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።
የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም ጸድቆ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።
አዋጁ በሀገሪቱ ያለውን የቤት ኪራይ ችግር ለመፍታት እንዲሁም፣ ፍትሃዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማህበረሰቡ ኑሮና በአጠቃላይ ሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ላይ የሚፈጥረውን ጫና ከግምት በማስገባት መዘጋጀቱ በሰነዱ ላይ ተቀምጧል።
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አዋጁን ተከትሎ የአከራይና ተከራይ ሕጋዊ ውል በማዘጋጀት ከሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ምዝገባ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ኢዜአ በአዲስ አበባ ያለውን የምዝገባ ሂደት ምን ይመስላል? በሚል በለሚ ኩራና በጉለሌ ክፍለ ከተሞች ቅኝት አድርጓል።
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የሚኖሩት ተከራዮች ወይዘሮ እናኒ ወልደ ጊዮርጊስና አቶ አብርሃም ታምራት ውል መፈጸሙ በተከራይ ላይ የሚደረግ አላግባብ ጭማሪን ጨምሮ እንግልቶችን የሚያስቀር ነው ብለዋል።
በጉለሌ ክፍለ ከተማ የሚገኙት ተከራይ ወይዘሮ አዲስ ታዬ እና አከራይ የሆኑት አቶ ሰለሞን ሸንቁጥ ሕጋዊ ውሉ የሁለቱንም ወገኖች መብት የሚጠበቅና ጥሩ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉት ውል በሚፈራረሙበት አንዳንድ ወረዳዎች ያለ መጨናነቅ እንዲፈታ ጠይቀዋል።
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የወረዳ 14 ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚዛን ኪዳኔ ጽህፈት ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ምዝገባ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ምዝገባው ይፋ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ዜጎች ወደ ጽህፈት ቤቱ በመምጣት እየተመዘገቡ መሆኑን አመልክተዋል።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 8 ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ በኃይሉ ምወድህ ወረዳው ከውሉ ጋር በተገናኙ ያሉ ብዥታዎችን ለማጥራት ግንዛቤ የመፍጠር ስራን ማከናወኑን ተናግረዋል።
ዜጎች በአገልግሎት አሰጣጡ መጉላላት እንዳይደርስባቸው በቴክኖሎጂ የተደገፈ ምዝገባ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለው መጨናነቅ ለመፍታት ከሰኞ እስከ አርብ ምሽትን ጨምሮ ቅዳሜና እሁድን ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ከሰኔ 1 እስከ 30/2016 ዓ.ም በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የግል ቤት አከራዮች ከተከራዮቻቸው ጋር ህጋዊ ሰነዶቻቸውን ይዘው በመቅረብ ምዝገባ እንዲያደርጉ የጊዜ ገደብ አስቀምጦ ነበር።
ይሁንና በተቀመጠው ጊዜ ምዝገባውን ለማጠናቀቅ አዳጋችና ከማህበረሰቡ በመጡ በርካታ ጥያቄዎች መሰረት የምዝገባ ጊዜው እስከ ሐምሌ 24/2016 ዓ.ም መራዘሙን ቢሮው ትናንት ማሳወቁ የሚታወስ ነው።