ቀጥታ፡

የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮችን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት መሰረት የሚጥል ነው

 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2016(ኢዜአ)፦ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት መሰረት የሚጥል መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ ሱሉልታ በሚገኘው የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲ እና የአደጋ ስጋት አመራር ረቂቅ አዋጅ ዝግጅትን አስመልክቶ ገለጻ አድርጓል።

በገለጻው ላይ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር)፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ(ዶ/ር) እና የኮሚሽኑ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የቋሚ ኮሚቴው አባላት ተገኝተዋል።


 

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ፖሊሲው በየካቲት ወር 2016 ዓ.ም ጸድቆ ስራ ላይ መዋሉን አስታውሰዋል።

የአደጋ ስጋት አመራር ፖሊሲ መጽደቁን ተከትሎም ተቋማዊ የስራ ማስፈጸሚያና የማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በዝግጅት ሂደት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚሁ ጊዜ በኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር የፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ነሲቡ ያሲን፥ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲ ይዘትና ምንነትን ለውይይት መነሻነት አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በለጋሽ አካላት የተንጠለጠለ የአደጋ ምላሽ አሰጣጥ ሂደትን ትከተል እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህም ከተረጅነት የተላቀቀ የአደጋ ምላሽ አሰጣጥ አካሄድን መከተል እንደሚገባ በመገንዘብ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲ ተቀርጾ ስራ ላይ መዋሉን ገልጸዋል።


 

ፖሊሲውም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት የሚከሰቱ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሃቆችን ከግምት በማስገባት በራስ አቅም ለአደጋ ምላሽ የመስጠት አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ ተመላክቶበታል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በ2030 ዓ.ም ለአደጋ ስጋት የማይበገር ማህበረሰብን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት መሰረት እንደሚሆን አስረድተዋል።

የሰብዓዊ አገልግሎት፣ ዘላቂ ልማትና የሰላም ጥምረትን በማረጋገጥ ዕውቀት መር በራስ አቅም አደጋን ምላሽ የሚሰጥ ተቋም ለመገንባት የማሻሻያ እርምጃ መወሰዱንም አንስተዋል።

በገለጻው ላይ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ፖሊሲ እና የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ዝግጅት ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል።


 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም