አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እየተፈተነ ላለው ሶማሌ ክልል ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው- ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እየተፈተነ ላለው ሶማሌ ክልል ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው- ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2016 (ኢዜአ)፦አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እየተፈተነ ላለው ሶማሌ ክልል ፋይዳው ዘርፈ ብዙ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ተናገሩ።
ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተተከሉ ችግኞች ከአካባቢ ጥበቃ ፋይዳቸው ባሻገር ለክልሉ ከተሞች ውበትና ገጽታ እንዳላበሱም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ለኢዜአ እንዳሉት አረንጓዴ አሻራ በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እየተፈተነ ላለው የሶማሌ ክልል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።
በዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ገቢራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የክልሉ መንግስት በየዓመቱ ትኩረት አድርጎ ሲሰራበት መቆየቱን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታትም ከክልሉ ቆላማ የዕጽዋት ብዝሐ ሕይወት ጥበቃ ባሻገር በከተሞች ላይ ተጨባጭ ለውጥ ያመጡ የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በከተሞች የደን ሽፋን በማሳደግ አረንጓዴ አሻራ አየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል ካለው ፋይዳ ባሻገር በከተሞች ውበት እና ገጸታ ላይ ሰፊ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።
በክልሉ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በስፋት ከተከናወነባቸው ከተሞች መካከል የጎዴ፣ የቀብሪ ደሀር እና ደገሀቡር ከተሞች ይገኙበታል።
የጎዴ ከተማ ከንቲባ አቶ አብዱላሂ አሊ እንደሚሉት ጎዴ ከተማ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በመሰረተ ልማትና በኢንቨስመንት ከፍተኛ መነቃቃት ላይ ከመሆኗ ባሻገር በከተማ ውበትና ጸዳት ሰፊ ስራዎች ተከናውነዋል።
አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ጋር በማስተሳሰር ለወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ለከተማዋ ውበት፣ ለህዝብ መዝናኛ የሆኑ አረንጓዴ ቦታዎች መልማታቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ለረዥም ዓመታት በሰላም እጦት ሳቢያ የግጭት ማዕከል የነበረችው ቀብሪደሃር ከተማ በአሁኑ ሰዓት አረንጓዴ ገጽታን እየተላበሰች መሆኗን የከተማዋ ከንቲባ ኢንጅነር አብዱራዛቅ አዊል ተናግረዋል።
የደገሀቡር ከተማ ስራ አስኪያጅ አቶ በሽር የሱፍ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለከተማቸው አዳዲስ መልክ በማላበስ ጽዱ፣ ውብና ማራኪ ከተማ እንድትሆን ማስቻሉን ገልጸዋል።