የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ለመስጠት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን-ዩኒቨርሲቲዎች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2016(ኢዜአ)፦ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና የሚፈተኑ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስፈተን የሚያስችላቸውን  የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በማከናወን ላይ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ገለጹ፡፡

የ2016 የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ከሐምሌ 3 እስከ ሀምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ለማኅበራዊ እና ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች እንደሚሰጥ ይታወቃል።

የትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናውን 701 ሺህ 489 ተማሪዎች እንደሚወስዱ እና ለፈተናውም ስኬታማነት በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን መግለጹ ይታወሳል።

ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናውን በወረቀትና በኦንላይን ለመስጠት የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውንም እንደዚሁ።

ኢዜአ ፈተናው ከሚሰጥባቸው ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እና የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲን አነጋግሯል፡፡

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ደረጀ እንግዳ የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በወረቀትና በቴክኖሎጂ በተደገፈ መልኩ እንደሚሰጥና ለዚህ የሚረዳ በቂ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። 

በዩኒቨርሲቲው ከ16 ሺህ የማያንሱ የማህበራዊና የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ፈተናቸውን ይወስዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል ከ1ሺህ በላይ ተማሪዎች ፈተናውን በኦንላይን እንደሚፈተኑ ተናግረዋል።

የፈተና ሂደቱን የተሳካ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው የማደሪያ ፣ የመፈተኛ ቦታዎችን የማመቻቸት እንዲሁም የመመገቢያ ሁኔታን ከወዲሁ የማስተካከል ስራ በማከናወን ላይ መሆኑን አብራርተዋል።


 

የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሀነመስቀል ጠና በበኩላቸው ዘንድሮ የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከ 3ሺ 800 ያላነሱ የተፈጥሮ እና የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ግቢ እንደሚፈተኑ ተናግረዋል።

ቅድመ ዝግጅትን በተመለከተ የተማሪዎችን የመኝታና፣ ጥናት የሚያደርጉበትን የቦታ እና የግብአት ሁኔታዎችን ማመቻቸት ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።

የፈተና አሰጣጥ ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን ዩኒቨርሲቲው ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

 ዶክተር ደረጀ ሀገር አቀፍ ፈተናው ተማሪዎች በእውቀት ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ራሳቸውን የሚፈትሹበት በመሆኑ ያለምንም መጨናነቅ እንዲዘጋጁ አስገንዝበዋል ።

ሀገር አቀፍ ፈተናው ወደ ሌላኛው የትምህርት ምዕራፍ የሚያሸጋግራቸው በመሆኑ ተማሪዎች ያለምንም መጨናነቅ በስነ ልቦና ዝግጁ ሆነው እንዲመጡ ዶክተር ብርሀነመስቀል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በተለይም በኦንላይን የሚፈተኑ ተማሪዎች ራሳቸውን ለፈተናው ዝግጁ ከማድረግ ባለፈ ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ የሚያሳስባቸው ነገር ሊኖር እንደማይገባ አስገንዝበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም