ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለዘላቂ ሰላምና ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡ የሚያስችል ውይይት እያካሄዱ ነው

ሐረር፤ ሰኔ 28/2016 (ኢዜአ)፦ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት ላይ የድርሻቸውን ሚና ለመጫወት የሚያስችል ውይይት በሐረር ከተማ እየተካሄደ ነው።

ውይይቱ " ለሀገራችን ሰላምና ብልፅግና የዲያስፖራው ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ ነው  እየተካሄደ ያለው ።

26ተኛ ዓለም አቀፍ  የሐረር ቀን ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ እየተካሄደ የሚገኘው ውይይት አላማ በመላው ዓለም የሚገኙ የክልሉ ተወላጆችና ወዳጆች በሀገርና በክልላቸው የተጀመሩትን  ሁለንተናዊ የሰላም እና የልማት ጉዞ ለማሳካት እያደረጉ የሚገኙትን አስተዋፅኦ ለማሳደግ ነው።



ከመላው ዓለም በዓሉን ለማክበር የመጡ ኢትዮጵያውያንና የሁለተኛው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢንቨስትመንት ሆነ በሌሎች በሚሳተፉባቸው መስኮች  ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ምችችት ለመፍጠርም ያለመ መሆኑ ተመላክቷል ። 

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይነህ አቅናው ለኢዜአ እንደገለፁት ፤ ውይይቱ ከዚህ በተጨማሪ የዲያስፖራው ማህበረሰብን የእርስ በርስ ግንኙነትና ከሀገራቸው ጋር ያላቸውን ትስስር ለማጠናከር ያግዛል።

በውይይቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ብርቱኳን አያኖ፣  የሐረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም፣የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመርና ሌሎች የፌደራልና የክልል  መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።

በሲምፖዚየሙ ላይ አምባሳደር ብርቱኳን አያኖ ለዲያስፖራው መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሲምፖዚየምሙ ዲያስፖራዎችና በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም