ቀጥታ፡

የስርዓተ ምግብ ልማት ሰብዓዊ ድጋፍና የሰላም ግንባታ መመሪያና ፍኖተ ካርታ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የስርዓተ ምግብ ልማት፣ ሰብዓዊ ድጋፍና የሰላም ዘላቂ መፍትሔ መመሪያና ፍኖተ ካርታ ይፋ ሆኗል።

የልማታዊ ፕሮግራም፣ የሰብዓዊ እርዳታና የሰላም ቅንጅት የሶስትዮሽ መመሪያና ፍኖተ ካርታ ይፋ ሆኗል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬሕይወት አበበ፤ የስርዓተ ምግብ ፍላጎትን ለማሟላት የተቀናጀ አካሄድና አሰራርን መከተል አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ መንግስት በሌማት ትሩፋትና የግብርና ምርታማነት ዘርፎች የዜጎችን የምግብና ስርዓተ ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የልማት፣ የሰብዓዊ ድጋፍና የሰላም ግንባታ ተግባራት በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ ለመምራትም መመሪያና ፍኖተ ካርታው ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በዘላቂ የልማት መርሃ ግብሮች ለማቋቋም አይነተኛ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር)፤ የተሻለ ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የተዘጋጀው መመሪያና ፍኖተ ካርታ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ቱሩፋት፣ በኩታ ገጠም የግብርና ልማት እና የስራ ዕድል ፈጠራ መንግስት ያስመዘገበውን ስኬት ለማስቀጠል አጋዥ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የስርዓተ ምግብ ማሳደግ ንቅናቄን ዋና የልማትና ዕድገት አጀንዳ በማድረግ እስከ 2022 ዓ.ም የስርዓተ ምግብ ችግሮችን ለመግታት እየሰራች መሆኗን አንስተዋል።

የሶስትዮሽ መመሪያና ፍኖተ ካርታ ይፋ በተደረገበት ሥነ-ስርዓት ላይ በኢትዮጵያ የአክሽን አጌይነሰት ሃንገር ቢሮ ኃላፊ ቻርልሰ ኦሴይ፣ የሴቭ ዘ-ችልድረን ዋና ኃላፊ ድራጋና ስትሪኒች እና ሌሎችም አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም