ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሪቶሪያው ስምምነትን ተከትሎ የሰጡት ማብራሪያ በተጨባጭ በተግባር የተገለፀ ነው - አስተያየት ሰጪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሪቶሪያው ስምምነትን ተከትሎ የሰጡት ማብራሪያ በተጨባጭ በተግባር የተገለፀ ነው - አስተያየት ሰጪዎች
አክሱም/ሸረ እንዳስላሴ/ ፤ ሰኔ 27/2016(ኢዜአ)፦ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለተወካዮች ምክር ቤት የፕሪቶሪያው ስምምነትን ተከትሎ በተከናወኑ ተግባራት ዙሪያ የሰጡት ማብራሪያ ትክክለኛና በተግባር የተገለፀ ነው ሲሉ የአክሱምና የሽሬ እንዳስላሴ ከተሞች ነዋሪዎች ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህ ወቅት የፕሪቶሪያው ሥምምነት ግጭትን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት የባህል ለውጥ የመጣበት መሆኑን ገልፀዋል።
ሥምምነቱ ጥሩ ድል መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በክልሉ ባንክ፣ አየር መንገድ እና ስልክን ጨምሮ ሌሎች በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ ሥራ መመለሳቸውን ተናግረዋል።
የተፈናቀሉ ሰዎች በመመለስም ጥሩ ጅምር መኖሩን አንስተዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአክሱምና የሽሬ እንዳስላሴ ነዋሪዎችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሪቶሪያውን ስምምነት አስመልክተው የሰጡት ማብራሪያ ትክክለኛና ተቋማት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውና የተጀመሩ የልማት ስራዎች በተግባር እየታዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአክሱም ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሮማን ልኡል ከፕሪቶርያው የሰላም ሰምምነት ወዲህ በትግራይ ክልል በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተከናውነዋል ማለታቸው በተግባር እየታየ ነው ብለዋል።
ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የአክሱም አፄ ዮሃንስ አራተኛ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ የስልክ፣ የኤሌትሪክ ሃይል እና የባንክ አገልግሎቶች በተሟላ ሁኔታ መጀመራቸው ለተሰጠው ማብራሪያ ትክክለኛ መገለጫዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ነዋሪዋ አክለውም ''ጦርነት ቀጣይ እንዳይሆን በምክክር ልናቆመው ይገባል ማለታቸው የመንግስትን ሆደ ሰፊነትና ሰላምን ለማፅናት ያለውን ቁርጠኝነትን ያሳያል'' ብለዋል።
የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነትን ለመተግበር የፌዴራል መንግስት እያሳየ የሚገኘውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ኪሮስ በርሄ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፕሪቶርያው የሰላም ሰምምነት አፈፃፀም ዙሪያ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ መንግስት ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የተጠናከረ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ስለተገነዘቡ መደሰታቸውን ገልፀዋል።
ከሶስት ዓመታት በላይ ከቀያቸው ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የቆዩ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለሱ ሂደት መጀመሩ ከሰላም ስምምነቱ የተግባር መገለጫዎች አንዱ ማሳያ እንደሆነም ወይዘሮ ኪሮስ ጠቁመዋል።
የአክሱም ከተማ ነዋሪ አቶ ሐድሽ ግደይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮንትሮባንድ ህገወጥ እንቅስቃሴን አስመልክተው የሰጡት ማብራሪያ "የድርጊቱን አፈፃፀም በትክክል መግለጻቸውና ሊወገድ እንደሚገባ አፅንኦት መስጠታቸው ተገቢ ነው" ብለዋል።
የሽሬ እንዳስላሴ ነዋሪ ኢንጂነር አብርሃ ካህሳይ በበኩላቸው፤ በሌማት ትሩፋት፣ በኮሪደር ልማት፣ በገበታ ለአገር፣ በገበታ ለትውልድና በአረንጓዴ አሻራ ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉት የልማት ስራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል። እነዚህ በሁሉም ክልሎች በስፋት መተግበር እንዳለባቸውም ተናግረዋል።