ከመንግስት ጎን ተሰልፈው ሰላምን በዘላቂነት ለማስጠበቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በደቡብ ወሎ ዞን ነዋሪዎች አስታወቁ - ኢዜአ አማርኛ
ከመንግስት ጎን ተሰልፈው ሰላምን በዘላቂነት ለማስጠበቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በደቡብ ወሎ ዞን ነዋሪዎች አስታወቁ
ደሴ፤ሰኔ 27/2016(ኢዜአ)፦ከመንግስት ጎን ተሰልፈው የአካባቢውን ብሎም የአገርን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በደቡብ ወሎ ዞን ነዋሪዎች አስታወቁ።
መንግስት ለዘላቂ ሰላምና ለአገር አንድነት የሰጠው ትኩረት የሚደነቅና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ይህንን የገለጹት ዛሬ በተካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ(ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ማብራሪያ ተከትሉ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ነው።
በዞኑ መቅደላ ወረዳ የማሻ ከተማ ነዋሪ አቶ ቴዎድሮስ አማከል፤ የኢትዮጵያ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ መንግስት በተደጋጋሚ ያሳየው ቁርጠኝነትና ፍላጎት አድንቀዋል፡፡
በዛሬው የምክር ቤት ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራ ማረጋገጣቸው ለችግሮቻችን መፍትሄ ሊያመጣ የሚችል ነው ብለዋል፡፡
እኛም ከመንግስት ጎን ተሰልፈን ሰላማችንና አንድነታችን ዘላቂ ለማድረግ የድርሻችንን እንወጣለን ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ በችግርም ውስጥ ቢሆን የተጀመሩ አስደናቂ ልማቶች አስደስተውናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በአልብኮ ወረዳ የሳልመኔ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ብርቱካን ይማም በበኩላቸው፤ ዛሬ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው ምላሽና ማብራሪያ ያሉብንን ብዥታዎች ያስተካከሉና ለሁለተናዊ እድገቶቻችን ተስፋ የሚሰጡ ናቸው ብለዋል፡፡
በተለይ ችግሮችን በውይይትና በምክክር ለመፍታት መንግስት ያሳየው ቁርጠኝነት እንደሚደነቅ አመልክተው፤ እኛም ለሰላማችን በዘላቂነት መጠበቅ ከመንግስት ጎን እንሰለፋለን ሲሉ አስታውቀዋል።
ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ሁሉም አካል ዝግጁ መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡
ለህዝብና ለሀገር የሚያስብና የሚቆረቆር ሁሉ ግጭት እንዲያቆምና ሀሳቡን ወደ ጠረጴዛ እንዲመጣ የጠየቁት ወይዘሮ ብርቱካን፤ መንግስትም በሆደ ሰፊነት የጀመረውን የሰላም ፍላጎት አጠናክሮ እንዲቀጠል አመልክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አንድነት ሰፍኖ የጀመርነው ሁለተናዊ ብልጽግና ዳር እንዲደርስ ታጣቂዎች ወደ ሰላም መጥተው መነጋገር አለባቸው ያሉት ደግሞ የወረኢሉ ከተማ ነዋሪ አቶ ዳውድ ጠጁ ናቸው፡፡
ለዚህም ዛሬ በምክር ቤቱ ስለ ሰላም፣ አንድነት፣ ልማት፣ ምክክርና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ(ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
የፕሪቶሪያ ሥምምነትም ግጭትን እንዲቆምና ወደ ልማት እንድንገባ እድል በመፍጠሩ ሙሉ በሙሉ ሊተገበር ይገባል ያሉት አቶ ዳውድ ፤ ችግሮችን በምክክር የመፍታት ባህላችንን ማጎልበት ይኖርብናል ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
እንደ አገር ብሎም እንደ ከተማችን የተጀመሩ ልማቶች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በሁሉም አካባቢ ዘላቂ ሰላም ቢፈጠር ታምር ሊሰራ እንደሚችል መገንዘብ ችለናል ብለዋል፡፡
አገራዊ ምክክሩ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባትና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚያስችል በመሆኑ ለዚህም ስኬታማነት የመንግስትን ቁርጠኝነት እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡