ተመራቂ ተማሪዎች በተግባርና ንድፈ ሃሳብ ያገኙትን ዕውቀት ለሀገር ዕድገትና ብልጽግና ማዋል ይጠበቅባቸዋል - ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ - ኢዜአ አማርኛ
ተመራቂ ተማሪዎች በተግባርና ንድፈ ሃሳብ ያገኙትን ዕውቀት ለሀገር ዕድገትና ብልጽግና ማዋል ይጠበቅባቸዋል - ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2016(ኢዜአ)፦ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ለሀገር ዕድገትና ብልጽግና ማዋል እንደሚጠበቅባቸው የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ አስገነዘቡ።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 67 ተማሪዎችን አስመርቋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የማዕድን ሚኒስትርና የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ፤ ለምርቃት የበቁ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታ ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ለሀገር ዕድገትና ብልጽግና ማዋል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በህይወት ዑደት የሚያጋጥሙ ውጣ ውረዶችን በመቋቋም ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ለህብረተሰብ ህይወት መሻሻል ተግባር ላይ ማዋል እንደሚኖርባቸውም አሳስበዋል።
የማህበረሰቡን ባህል፣ እሴትና ሥርዓት በማክበር ኢኮኖሚያዊ ለውጥ በሚያመጡ መስኮች ተሰማርተው ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በቅንነትና ታማኝነት ማገልገል እንደሚባቸውም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ደረጀ እንግዳ(ዶ/ር)፤ ምሩቃኑ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ የሚያስችል የንድፈ ሃሳብና የተግባር ክህሎት ስልጠና ሲከታተሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው የተማሪ ልማት ማዕቀፍ በማዘጋጀትና ከተለያዩ አጋር አካለት ጋር በመተባበር ከመደበኛ ትምህርት ባሻገር ሁለንተናዊ የስብዕና ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሚሰጣቸውን ትምህርቶችም ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑንም አንስቷል፡፡
በዚህም የመውጫ ፈተና ከወሰዱ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች መካከል 97 ነጥብ 6 በመቶው የማለፊያ ውጤት ማስመዝገባቸውን አስታውቀዋል።
ዩኒቨርሲቲው የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ገበያ የሚፈልገውን የሰው ኃይል ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የማህበረሰቡን ችግሮች በጥናትና በምርምር የሚፈቱ ምሁራንን በማፍራት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ተመራቂዎች መካከል ሰለሞን ዳንኤል፤ ጠንክሮ በመስራቱ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቦ ለምርቃት መብቃቱን ገልጿል።
በቀጣይም በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ያገኘውን በንፈ ሃሳብና ተግባር የተደገፈ ዕውቀትና ክህሎት ተግባር ላይ በማዋል የመንግስትን የስራ ዕድል ሳይጠብቅ ለሀገር ዕድገት እንደሚሰራ ተናግሯል።
በተመረቅኩበት የትምህርት ዘርፍ ተወዳዳሪና ስራ ፈጣሪ ሆኘ ሀገሬን እና ህዝቤን በታማኝነት አገለግላለሁ ያለችው ደግሞ ሌላኛዋ ተመራቂ ሄለን ይሳቅ ናት።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የማዕድን ሚኒስትርና የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የተመራቂ ቤተሰቦች፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።