ቀጥታ፡

በደም የጠበቅናትን ሀገር በኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማፅናት ግብርን በአግባቡ መክፈል ይገባል -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2016(ኢዜአ)፦በደም የጠበቅናትን ሀገር በኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማፅናት ግብርን በአግባቡ መክፈል ይገባል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡

ግብር ለሀገር ክብር ዓመታዊ የታክስና ጉምሩክ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ማጠቃለያ እና አዲስ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐግብር ተካሂዷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ጊዜ፤ የየትኛውም ሀገር መንግስት ኃላፊነቱን ለመወጣትና ለዜጎች የገባውን ቃል ለመፈጸም ታክስና ገቢ በብቃት መሰብሰብ አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የልማት ስራዎችን ለማሳካት የገቢ መሰብሰብ አቅምን እያሳደገ መምጣቱንም ነው የተናገሩት።

የታክስና ጉምሩክ ህግ ተገዥነትን ለማሳደግ የተለያዩ ንቅናቄዎች መከናወናቸውን አንስተው፤ በግብር ለሀገር ክብር ንቅናቄ የህብረተሰቡን ግብር የመክፈል ሞራል የሚያሳድጉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የተሟላ ክብር ያላት እና እጇን ለልመና የማትዘረጋ ሀገር ለማድረግ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ትልሞችን ለማሳካት ታክስና ቀረጥን በአግባቡ  መሰብሰብ ወሳኝ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያዊያን የሀገር ዳርድንበርና ሉዓላዊነትን በጀግንነት እንዳስከበሩ አንስተው፤ በደም የጠበቅናትን ሀገር በኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማፅናት ግብርን በአግባቡ መክፈል ያስፈልጋል ነው ያሉት። 

ኢትዮጵያ ዓመታዊ በጀቷን በበቂ ሁኔታ ከሀገር ውስጥ ገቢ መሰብሰብ እንዳልቻለች ጠቅሰው፥ ግብር የመሰብሰብ ምጣኔ ከሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት አንጻር ያለው ድርሻ ከነጠላ አሃዝ አልበለጠም ብለዋል።

ከዚህ አኳያ ግብርን በታማኝነት መክፈል የዘመኑ ዓድዋ መሆኑንም አንስተዋል።

ዜጎች ግብር በመክፈል ሀገራቸውን ከፍ ማድረግ እንዳለባቸው አንስተው፤  የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉ አካላት በሚያሰራጩት አሉባልታ ጆሮ ባለመስጠት ልማት ላይ ማተኮር እንደሚገባም ተናግረዋል። 

በመርሐ ግብሩ ለንቅናቄው መሳካት አስተዋፅኦ ላደረጉ የክልል ተቋማት እና ከተማ አስተዳደሮች ዕውቅና ተሰጥቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም