የኢትዮጵያ እድገት ለማስቀጠል ተመራቂ ተማሪዎች የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እድገት ለማስቀጠል ተመራቂ ተማሪዎች የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው
ባህርዳር/ደብረ ብርሃን/ ወልድያ፤ሰኔ 27/2016 (ኢዜአ)፡- ተመራቂ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው የኢትዮጵያን እድገት ለማስቀጠል የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተገለጸ።
ደብረ ብርሃን ፣ ወልዲያና እንጅባራ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎች ዛሬ አስመርቀዋል።
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ንጉስ ታደሰ (ዶ/ር) በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ እንደገለጹት፤ ተቋሙ ከመማር ማስተማሩ ስራ በተጓዳኝ ለምርምርና ለማህበረሰብ አገልግሎት ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ ነው።
ስራውን በመቀጠል ባለፉት ዓመታት በማህበራዊና በተፈጥሮ ሳይንስ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ያስተማራቸውን አንድ ሺህ 789 ተማሪዎች ዛሬ ማስመረቁን ተናግረዋል።
ለ16ኛ ዙር ካስመረቃቸው ከእነዚህ ተማሪዎች ውስጥ 436 ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ተመራቂዎችም በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም ስራ ፈጥረው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለማቻል መትጋት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የአገርን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስቀጠልም የድርሻቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአይሲቲና ድጅታላይዜሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን ዓለማየሁ(ዶ/ር) ፤ ተመራቂዎች የአገሪቱን ልማትና እድገት ለማጠናከር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በሚሰማሩበት የስራ ዘርፍ ሁሉ የማህበረሰቡን የመቻቻልና የአብሮነት እሴቶችን በማጠናከር ለአገር ሰላምና አንድነት እንዲሰሩም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በፋርማሲ የትምህርት ክፍል ተመራቂ ራዕይ ግርማ በሰጠችው አስተያየት፤ 3ነጥብ 9 ውጤት በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ በመሆኗ መደሰቷን ገልጻ ፤ ህዝቧን በሙያዋ ለማገልገል መዘጋጀቷን ተናግራለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ዓመታት ሲሰለጥናቸው የቆዩ 544 ተማሪዎችን ዛሬ አስመረቋል።
በዚህ ወቅት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አበበ ግርማ(ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር የዛሬ ተመራቂዎች ችግርን ተቋቁመው ሌት ከቀን በመትጋት ለውጤት መብቃታቸውን ገልጸዋል።
ይህም በቀጣይ የሚገጥማቸውን ፈተና አልፈው ትልቅ ደረጃ ላይ በመድረስ በአገራቸው ልማትና እድገት ላይ ለማዋል የሚያግዳቸው ነገር የሌለ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።
ከየኒቨርሲቲው ተመራቂዎች መካከል ዳዊት አስቻለው በሰጠው አስተያየት፤ ለዛሬው ስኬቴ ወላጆቼ፣ መምህሮቼና ማህበረሰቡ ባለውለታዬ በመሆናቸው በሰለጠንኩበት ሙያ በታማኝነትና በትጋት አገለግላለሁ ብሏል።
በሌላ በኩል የእንጅባራ ዪኒቨርሲቲም በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ከ690 በላይ ተማሪዎችን አስመረቋል።