ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የሁልጊዜም ፍላጎት ከጎረቤት አገራት ጋር በጋራ መልማትና ማደግ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የሁልጊዜም ፍላጎት ከጎረቤት አገራት ጋር በትብብር መልማትና ማደግ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ። 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 36ኛ መደበኛ ስብስባውን ዛሬ አድርጓል። 


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮችና የመንግሥት የሥራ አፈጻጸምን በተመለከተ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጎረቤት አገራት ተኮርና ከአገራቱ በጋራ መልማትና ማደግ ላይ መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ለጎረቤት አገራት የምትሰጠውን ትኩረት በተለያዩ ማሳያዎች አንስተዋል።

ከሱዳን ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሱዳን ሕዝብ ግጭት የማይፈልግ ሰላም ወዳድ ከኢትዮጵያ ጋር ጥልቅ የሆነ ማኅበረሰባዊ ትስስር እንዳለው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ መንግሥት በሱዳን ያለው ግጭት ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያገኝና ለማንም ሳይወገን ገለልተኛ በሆነ መልኩ እንዲፈታ ፍላጎት አላቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሱዳን ችግር ፍትሃዊ በሆነ መንገድና የሱዳናውያንን አንድነት በሚያጠናክር መልኩ እንዲፈታ እየሰራች እንደምትገኝና ይህንንም አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሶማሊያ ጋር በተገናኘ ባነሱት ሃሳብም፤ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ወንድማዊ የሆነ ትብብር እንዳላትና ለአገሪቷ እድገት፣ ሰላምና ብልጽግና ዋጋ መክፈሏን አውስተዋል።

ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት፣ አንድነትና የግዛት አንድነት እንደምታከብር ጠቅሰው ሰላሟን አጥብቃ እንደምትሻም ጠቁመዋል። 

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው ሥምምነት የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የማድረግ አካል እንጂ የሶማሊያን የግዛት አንድነት እንደ መጣስ ሊታይ እንደማይገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ሕጋዊ ጥያቄና ብሔራዊ ፍላጎት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቅ ኢኮኖሚና ሕዝብ ያላት አገር የባህር በር አጥታ ተዘግታ መቆየት አትችልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከሥምምነቱ ጋር ያሉ ጉዳዮችን ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርግ መልኩ በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኗን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የሁልጊዜም ፍላጎት በቀጣናዊ ትብብር ከጎረቤት አገራት ሰላም እንዲመጣ በትብብር መሥራት፣ አብሮ ማደግና በጋራ መበልጸግ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፍሪካና በቀጣናው አገሪቷን ወደ ጎን ትቶ የሚደረግ ጉዞ ውጤታማ እንደማይሆንና በትብብር ማደግ ብቸኛው አማራጭ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም