ቀጥታ፡

የ2017 የፌዴራል በጀት 971 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ሆኖ ፀደቀ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2016(ኢዜአ)፦የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ለ2017 የቀረበውን 971 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የመንግሥት በጀት አፅድቋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል። 

የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀትን አስመልክቶ ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርቧል።

ምክር ቤቱን የቀረበለትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ አዳምጦ ረቂቅ በጀቱን በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።


 

የፀደቀው 971 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ከ2016 በጀት አንጻር የ169 ነጥብ 56 ቢሊዮን ብር ወይም የ21 ነጥብ 1 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተጠቁሟል።

ከዚህም ውስጥ 451 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ፣ 283 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ወጪዎች እና 236 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ለክልል መንግሥታት የበጀት ድጋፍ የተመደበ ነው።

ለክልል መንግሥታት ከተመደበው የበጀት ድጋፍ 14 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ እንደሚውል ተገልጿል።

ከተያዘው በጀት ውስጥ 502 ቢሊዮን ብር  ከገቢ ግብር ለመሰብሰብ መታቀዱንና በአጠቃላይ 563 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር  ታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች ለማሰባሰብ መታሰቡን ጠቁመዋል።

ከተመደበው በጀት 139 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብሩ ለእዳ ክፍያ ይውላል ነው የተባለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም