ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መንግስት ምንም ዓይነት መንግስታዊ ሌብነት አይፈፅምም-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መንግስት ምንም ዓይነት መንግስታዊ ሌብነት የማይፈፅም መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መንግስት ሙስናን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየወሰዳቸው ስላሉ እርምጃዎች ላቀረቡት ጥያቄ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሌብነት "ነቀርሳ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሌብነት አካሄድ የሀገርን የልማት ጉዞ የሚያደናቅፍ የእድገት ጠንቅ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም የሌብነት ወንጀል ፈፅመው የተገኙ በርካታ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በመዋል በርካታ ሃብት ማስመለሱንም ጠቅሰዋል።

የተቋማት ማሻሻያና የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም የተጀመረውም መንግስት ሌብነትን ለመከላከል ባለው ቁርጠኝነት ነው ብለዋል።

የንብረት ማስመለስ አዋጅን ለማውጣት የታሰበበት ዓላማም ምንጩ ያልታወቀ ከፍተኛ ሀብት የሚያንቀሳቅሱ አካላትን የሀብት መነሻ ለማጣራትና በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ህዝቡ መገንዘብ ያለበት ህጎች የሚወጡት ሌቦች ላይ እርምጃ ለመውሰድ መሆኑን አብራርተዋል።

 የኢትዮጵያ መንግስት ምንም ዓይነት መንግስታዊ ሌብነት እንደማይፈፅምና ሀብትን ለልማት ከማዋል ውጭ ወደ የትኛውም ያልተፈለገ ሁኔታ እንደማይወስድ አረጋግጠዋል።

ለሌብነት የማይመች አሰራርን መዘርጋትና ለህዝቡ ሌብነት የሀገር ነቀርሳ መሆኑን ማስተማር እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል::

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም