ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርኃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 67 ተማሪዎችን አስመረቀ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2016(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ  በመጀመሪያ፣  በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 67 ተማሪዎችን አስመረቀ።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ  የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ኃብታሙ ተገኝን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የተመራቂ ቤተሰቦች፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት  ደረጀ  እንግዳ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ ተመራቂ ተማሪዎች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ጥራት ያለው የንድፈ ኃሳብና የተግባር ትምህርትን ሲሰጣቸው ነበር።

ዩኒቨርሲቲው ካስመረቃቸው 1 ሺህ 67 ተማሪዎች መካከል 27 በመቶው ሴቶች መሆናቸውን ገልጸው በዘንድሮው ዓመት ዩኒቨርሲቲው ለመውጫ ፈተና ካስቀመጣቸው የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ውስጥ    97 ነጥብ 6 በመቶው የማለፊያ ውጤት ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ገበያው የሚፈልገውን የሰው ኃይል ለማፍራት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰቡን ችግሮች በጥናትና በምርምር ሊፈቱ የሚችሉ ምሁራንን ለማፍራት እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም