በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከ10 በመቶ በላይ ዕድገት ተመዝግቧል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከ10 በመቶ በላይ ዕድገት ተመዝግቧል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2016(ኢዜአ)፦በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከአምራች ኢንዱስትሪው ከ10 በመቶ በላይ ዕድገት በማስመዝገብ አመርቂ ውጤት መገኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ እየተካሄደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ካስመዘገበቻቸው ስኬቶች አንዱ የኢንዱስትሪ እምርታ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ጨምሮ የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ በተወሰዱ እርምጃዎች ዘንድሮ በአምራች ዘርፉ ትልቅ ስኬት መመዝገቡን ተናግረዋል።
በዚህም ዘርፉ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 10 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡንም ጠቅሰዋል።
በዘንድሮው ዓመት 390 ፋብሪካዎች ወደ ስራ መግባታቸውንም አስታውሰዋል።
በትግራይ ክልል 217 ፋብሪካዎች ወደ ስራ መመለሳቸውን ገልጸው፤ በአጠቃላይ የፋብሪካዎች ምርታማነት መጨመር በተኪ ምርቶች እና በወጪ ምርቶች ላይ ትልቅ ውጤት መመዝገቡን ነው ያነሱት።
በነባር ሲሚንቶ ፋብሪካዎች 30 በመቶ የምርት ዕድገት መመዝገቡን ጠቅሰው አሁን ያለውን ሀገራዊ የሲሚንቶ ምርት 50 በመቶ የሚሸፍን አዲሱ የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ በቅርቡ ይመረቃል ብለዋል።
በመንግስት በዘርፉ ላይ ያደረጋቸውን ድጋፎች ለኢንዱስትሪዎች ምርታማነት ትልቅ ዕገዛ ማድረጉንም ገልጸዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለአምራቾች ከማቅረብ ባሻገር የነጻ ንግድ ቀጣናዎችን በማጠናከር ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍላጎት እያመጣ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
ዘንድሮ የተገኘውን ዕድገት በማስቀጠል ቀጣይነት ያለው ፈጣን ኢኮኖሚ ለማረጋገጥ እንደሚቻልም ነው ያነሱት።