ቀጥታ፡

የፋይናንስ ዘርፍ መረጋጋት በብዙ አመላካቾች መሻሻል አሳይቷል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2016(ኢዜአ)፦ የፋይናንስ ዘርፍ መረጋጋት በብዙ አመላካቾች መሻሻል ማሳየቱንና የዘርፉ እድገት ጤናማ የሚባል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ባንኮች ከውጭ ባንኮች ጋር ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችላቸውን የተወዳደሪነት አቅም እንዲገነቡም አሳስበዋል።


 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 36ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌዴራል መንግሥቱ የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ በመስጠት ላይ ይገኛሉ። 

በዚህም መንግሥት በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎች ለውጥ እያመጡ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የዚሁ ለውጥ ማሳያ አንዱ የሆነው በፋይናንስ ዘርፉ እየታየ ያለው መረጋጋት እንደሆነ ጠቅሰው በዓለም አቀፍ አመላካቾች ከፍተኛ መሻሻል እንዳለ አመልክተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የማይመለሱ ብድሮች ምጣኔ 5 በመቶ እንደሆነና በኢትዮጵያ ይህ አሃዝ 4 ነጥብ 5 በመቶ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰዋል።

ከሚሰበሰብ ገቢ 80 በመቶው ለግሉ ዘርፍ እንደሚመደብና ይህም ዘርፉን ለማነቃቃት ያለው ፋይዳ ወሳኝ እንደሆነ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የነበሩ 17 ባንኮች አሁን ላይ ወደ 32 ማደጋቸውንና የዚህ ዓመት ትርፋቸው ከባለፈው ዓመት አንጻር ከ24 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል።

5 ሺህ 400 የነበሩት የባንኮች ቅርንጫፎች በአሁኑ ወቅት ከ12 ሺህ 800 በላይ መድረሳቸውንና 38 ሚሊዮን የነበረው የቁጠባ ሂሳብ ደብተር አሁን ላይ ከ100 ሚሊዮን መሻገሩን ተናግረዋል።

ይህም በርካታ ዜጎችና ተቋማት ወደ ባንክ ኢንዱስትሪው እየገቡ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በሞባይል የገንዘብ ዝውውር አማራጭ የሚጠቀሙ ዜጎች ቁጥር 47 ሚሊዮን መድረሱንም አንስተዋል። 

መንግሥት የአሰራር ማዕቀፎችን ጨምሮ የውጭ ባንኮች በባንክ ዘርፉ እንዲሰማሩ የሚያስችሉ ተግባራት በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ባንኮች ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት የአሰራርና የሰው ኃይል አቅማቸውን፣ የቴክኖሎጂ አቅማቸውንና ተደራሽነታቸውን ይበልጥ በማጎልበት የተወዳዳሪነት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ጥሪ አቅርበዋል። 

የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የዘርፉን አሰራር ማዘመንና የተወዳዳሪነት አቅም ለማጎልበት እንድሚያግዝም አክለዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም