በታዳሽ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ለማስፋፋት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በታዳሽ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ለማስፋፋት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2016(ኢዜአ)፦ በታዳሽ ኃይል ለሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ስታንዳርድ እንዲዘጋጅ በማድረግ በአገሪቱ እንዲስፋፉ እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ከሰኔ 26 እስከ 28/2016 ዓ.ም የሚካሄደው ኢትዮ-ኦቶሞቲቭ፣ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ኤክስፖን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ዛሬ መርቀው ከፍተውታል።
በኤክስፖው በኦቶሞቲቭ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዘርፍ የተሰማሩ ዓለም አቀፍ የተሽከርካሪ አምራቾች፣ መገጣጠሚያ፣ ወኪል አስመጪዎችና በዘርፉ የተሰማሩ አቅራቢዎች ተሳትፈዋል።
በአየርና በየብስ ትራንስፖርት የተሰማሩ ኩባንያዎችና የሎጀስቲክስ አስተላላፊዎችም እየተሳተፉ ነው።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ፤ በኤክስፖው የዘርፉ ተዋናዮች የቴክኖሎጂ ፈጠራ ምርትና አገልግሎታቸውን እንዲያስተዋውቁ ታልሞ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዘርፍ ለአገር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መሳለጥ የሚጠበቅበትን አይተኬ ሚና መወጣት የሚያስችለውን የአሰራር ማሻሻያ ተድርጎ እየተሰራበት እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በዚህም በታዳሽ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በማስገባት ለረጅም ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩ ተሽከርካሪዎችን መተካት የሚስችል ስትራቴጂክ ፖሊሲ ሥራ ላይ እንዲውል መደረጉን ተናግረዋል
በኢትዮጵያም ዘመናዊ ትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታትም ወጥ የሆነ የአሸከርካሪ ምዘና በማዘጋጀት የዜጎችን ህይወት እየቀጠፈ የሚገኘውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
በታዳሽ ኃይል ለሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ስታንዳርድ እንዲዘጋጅ በማድረግ በአገሪቱ እንዲስፋፉ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሰጠኝ እንግዳው፤ ኤክስፖው ኩባንያቸው የሚገጣጥማቸውን በታዳሽ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ለማስተዋወቅ ዕድል የፈጠረ ነው ብለዋል።
በኤክስፖው ላይ ወጭ ቀጣቢና የአየር ብክለትን ለመቀነስ የሚያስችሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በአውደ ርዕዩ እያስተዋወቁ መሆናቸውን ገልፀዋል።
አጠቃላይ የትራፊክ አደጋ መቀነስ ቴክኖሎጂ አስመጪው ዑመር ያሲን፤ የትራፊክ አደጋን መቆጣጠር የሚያስችሉ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደአገር ቤት በማስገባት እያስተዋወቁ መሆኑን ገልጸዋል።