ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የተቀናጀ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ አጀንዳ ወሳኝና የሚደነቅ ነው - ፓብሎ ቬራ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የጀመረችው የተቀናጀ እርምጃ የሚደነቅ መሆኑን የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ አጋርነት ዓለም አቀፍ ዳይሬክተር ፓብሎ ቬራ (ዶ/ር) ገለጹ።

ኢትዮጵያ በፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ሥምምነት መሰረት በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዕቅድ የትግበራ መርኃ ግብርን ዛሬ ይፋ አድርጋለች።

በሁነቱ ላይ በበይነ መረብ መልዕክት ያስተላለፉት የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዓለም አቀፋዊ አጋርነት ዳይሬክተር ፓብሎ ቬራ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ የፓሪሱን ሥምምነት ወደ ተግባር በመቀየር አገራዊ ሚናዋን እየተወጣች ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚን በስኬት እየገነባች መሆኗ የሚደነቅ ወሳኝ አጀንዳ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለዚህም ስትራቴጂ ከማውጣት ባለፈ ከአምስት ዓመታት በፊት የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ የሰጠችውን ትኩረት አግዝፎ የሚያሳይ እንደሆነ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ሥምምነትን መሰረት በማድረግ እስከ ፈረንጆቹ 2030 ባሉት ዓመታት የሚተገበር የአየር ንብረት ለውጥ ተግባራዊ ምላሽ ዕቅድ አዘጋጅታ ይፋ ማድረጓም ሌላ እርምጃ ነው ብለዋል።

የዕቅዱ ትግበራ መርኃ ግብር በይፋ መጀመሩም  ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመው መርኃ ግብሩ በሁሉም የኢኮኖሚ መስኮችና በማኅበረሰብ ደረጃ የተቀናጀ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን መፍጠርን ያካተተ ነው ብለዋል።

በግብርና፣ በታዳሽ ሃይል፣ ደንና መሬት አጠቃቀም፣ ውሃ፣ በትራንስፖርት፣ በቆሻሻ አወጋገድ፣ በኢንዱስትሪና ሌሎችም መስኮች  በተቀናጀ መንገድ ውጤት ማምጣትን ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መንግስት ዕቅዱን ከ10 ዓመቱ መሪ የልማት ፍኖተ ካርታ፣ ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂና ሌሎችም ኢኒሼቲቮች ጋር በተጣጣመ መልኩ ለመተግበር ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጧል ነው ያሉት።

የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ትግበራ መርሐ ግብሩ ተፅዕኖን በመቋቋምና በመከላከል ረገድ ብዝሃ የትግበራ ሥልትን የሚከተል እንደሆነም ጠቁመዋል።

በመርኃ ግብሩ የመንግሥት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማትና ሌሎች አካላት ድርሻ በግልፅ መመላከቱን አንስተው፥ ይህም ሚናን በአግባቡ ለመወጣት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ የትግበራ መርሐ ግብር ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት 316 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

ለስኬቱ የኃብት ማሰባሰብ ስራ ትልቅ ክፍተት እንዳይፈጥር ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ድጋፍ በማድረግ ቁርጠኝነታቸውን እንዲያሳዩም ጠይቀዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዓለም አቀፍ አጋርነቱም የትግበራ መርኃ ግብሩ እንዲሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በፈረንጆች 2015 ፓሪስ ላይ በተፈረመው የአየር ንብረት ሥምምነት መሰረት አባል አገራት በየአምስት ዓመቱ የአገራቱን የላቀ ፍላጎት የሚያንፅባርቅ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዕቅድ ለማስገባት ተስማምተዋል። 

ኢትዮጵያ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የተሻሻለ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዕቅዷን ለተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፋዊ ሥምምነት ሴክሬታሪያት ከሁለት ዓመት በፊት አስገብታለች።

በዕቅዱ መሰረትም በ2022 ዓ.ም የ68 ነጥብ 8 በመቶ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ቅነሳን ለማሳካት ግብ አስቀምጣ ትግበራ ጀምራለች።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም