የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና የዲጂታል ግብይት ፕሮቶኮል ለዲጅታል የንግድ ዘርፍ ሰፊ እድል የሚፈጥር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና የዲጂታል ግብይት ፕሮቶኮል ለዲጅታል የንግድ ዘርፍ ሰፊ እድል የሚፈጥር ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2016(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና የዲጂታል ግብይት ፕሮቶኮል ለዲጅታል የንግድ ዘርፍ ሰፊ እድል የሚፈጥር መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
በሚኒስቴሩ እና የኢትዮጵያ የአይ ሲቲ ማኅበር ትብብር የተዘጋጀው በአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት የዲጂታል ግብይትን ለማካተት በሚያስችለው ፕሮቶኮልና ኢ-ኮሜርስ ላይ ያተኮረ አውደ- ጥናት ተካሂዷል።
በአውደ-ጥናቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን አለማየሁ(ዶ/ር)፤ የዓለም የግብይት ሂደት በፍጥነት ወደ ዲጂታል መቀየሩን ገልፀዋል።
በዚህ ረገድ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና የዲጂታል ግብይት ፕሮቶኮልም ለአህጉራዊ የምጣኔ ኃብት እድገት ጥሩ መሠረት የሚያኖር ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና የዲጂታል ግብይት ፕሮቶኮል ለዲጅታል የንግድ ዘርፍ ሰፊ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።
በመሆኑም በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና የአይ ሲቲ ዘርፉን የላቀ ፋይዳና ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ አረጋግጠዋል።
በሚኒስቴሩ የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ስዩም መንገሻ፤ የዲጂታል 2025 ስትራቴጂን መሠረት በማድረግ በአይ ሲቲ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶችን ለመደገፍ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በግሉ ዘርፍ በሚነሱ ጥያቄዎች ላይ በመመስረት አሠራሮች መዘርጋታቸውንም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ የአይ ሲቲ ማኅበር ፕሬዝዳንት ይልቃል አባተ፤ አውደ-ጥናቱ በያዝነው ዓመት የካቲት ወር ላይ በጸደቀው የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና የዲጂታል ግብይት ፕሮቶኮል አባሪዎች ላይ ለመምከር የተዘጋጀ ነው ብለዋል።