በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የኃይማኖት አባቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የኃይማኖት አባቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የኃይማኖት አባቶች የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱአለም ጥሪ አቀረቡ።
የሰላም ሚኒስቴር “የሃይማኖት ተቋሞቻችን ለዘላቂ ሰላማችን” በሚል መሪ ኃሳብ ከሁሉም ቤተ-ዕምነቶች ከተውጣጡ የኃይማኖት አባቶች፣ የኃይማኖት አስተማሪዎች፣ የፌዴራልና የክልል አመራሮች ጋር አገር አቀፍ ኮንፍረንስ አሂዷል።
የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም በዚሁ ጊዜ የኃይማኖት ተቋማት ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በጋራ መሥራትና የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነትም በአግባቡ መወጣት ይገባቸዋል ብለዋል።
ሰላም በሁሉም ኃይማኖቶች አስተምሮ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኃይማኖት አባቶች ተከታዮቻቸው ስለ ሰላም ይበልጥ በማስተማር ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።
ለዚህም በተለይም በየዕለቱ ከእምነቱ ተከታዩች ጋር በሚያደርጉት ኃይማኖታዊ አስተምሕሮ ውስጥ የሰላም ጉዳይን በማጎላት፤ በትኩረት ሊያስተምሩ እንደሚገባ ነው የጠቀሱት።
በዋናነትም በምእመናኑ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ተጠቅመው ማስተማርና አጥፊዎች ሲገኙም በመገሰጽ ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲያመሩ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል።
የኃይማኖት ተቋማት ብዝኃነትን በማስተናገድ ረገድ ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዙ በመሆናቸውም ብዝኃነት፣ አብሮነትና ፍቅርን በማስተማር ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ይህም ለዘላቂ ሰላም ግንባታም ድርሻው ከፍተኛ መሆኑን በመጠቆም።
የውይይቱ ተሳታፊ የኃይማኖት አባቶች በበኩላቸው፤ ሰላም ከሌለ መንፈሳዊም ሆነ ዓለማዊ ተቋማትን መምራት የማይታሰብ በመሆኑ ለሰላም ሁሉም በጋራ መሥራት አለበት ብለዋል።
ጥላቻና ጠብ ተገቢ ያልሆነና ግለሰብን፣ ማኅበረሰብን በድምሩም አገር የሚጎዳ መሆኑን የጠቀሱት የኃይማኖት አባቶች ለዘላቂ ሰላም በጋራ ልንቆም ይገባል ነው ያሉት።
የኃይማኖት አባቶች ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ችግሩን በቅጡ በመረዳት ለመፍትሄው ተባብሮ መሥራት እንደሚገባ ገልጸው ለዚህም የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
በውይይቱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች እንዲሁም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የመጡ የኃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።