በቀጣይ ጥቂት ዓመታት ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነውን የኮንስትራክሽን ዘርፍ ግብዓት በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በቀጣይ ጥቂት ዓመታት ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነውን የኮንስትራክሽን ዘርፍ ግብዓት በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2016(ኢዜአ)፦ በቀጣይ ጥቂት ዓመታት ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነውን የኮንስትራክሽን ዘርፍ ግብዓት በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ግርማ ኃብተማርያም በተከታታይ እየተስተዋለ ያለው የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ ንረት ለዘርፉ ተግዳሮት ከሆኑ ችግሮች ቀዳሚው መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህ ባለፈ ዘርፉ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዳይወጣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የግብዓት አቅርቦት ችግር ፈትነውታል ብለዋል።
ይህንንም ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ማኅበሩ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ፈተናዎችን ለመሻገር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፤ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ የተሰማሩ አካላቶች በተለያዩ ጊዜያት ከሚያነሷቸው ችግሮች ውስጥ የግብዓት አቅርቦትና የዋጋ ንረት ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ማነቆ የሆነውን የግብዓት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም የግብዓት አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ የተጀመረው ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸው መሰል ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም የግብአት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን የመሳብ፣ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ተግባራዊ ማድረግና ሌሎች ተግባራቶች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።