የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት 10ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባዔውን ሊያካሂድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት 10ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባዔውን ሊያካሂድ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት 10ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባዔ ሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጉባዔውን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።
የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መልአኩ እዘዘው እንዳሉት፤ የምክር ቤቱ 10ኛ ጠቅላላ መደበኛ ጉባዔ በቀጣዩ ሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
በጉባዔው ላይ ፕሬዝዳንት፣ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ እንደሚካሄድ ጠቁመው፤ ለዚህም ምርጫውን የሚያስተባብር ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ምክር ቤቱን እየመራ ያለው የዳይሬክተሮች ቦርድ በ2010 ዓ.ም. ተመርጦ ወደ ሥልጣን የመጣ መሆኑን አስታውሰው፤ ከዚህ ቀደም ቦርዱን የሚተካ ምርጫ በማካሄድ ፕሬዝዳንት፣ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዳይሬክተሮች ቦርድ ለመምረጥ የተደረገው ሙከራ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
በ2012 ዓ.ም በወቅቱ የነበረው የደቡብ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ማድረግ የማይችልበትን ምክንያት ጠቅሶ ለቀድሞ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አቤቱታ ማቅረቡን ጠቁመው፤ ሚኒስቴሩ አቤቱታውን በመቀበል የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ እንዳይካሄድ በደብዳቤ አግዶ መቆየቱን ተናግረዋል።
በ2013 ዓ.ም. በተመሳሳይ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ ቢገባም፤ በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘ ጠቅላላ ጉባዔው እንዳይካሄድ የተወሰነው ውሳኔ በመጽናቱ ምክንያት ጠቅላላ ጉባዔው ሳይካሄድ መቆየቱን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የምክር ቤቱ አባላትን ዝርዝር ከማሳወቅ፣ ዓመታዊ መዋጮ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ መሥፈርቶች ጋር በተያያዘ መዘግየቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህም ችግሮች ጠቅላላ ጉባዔው በወቅቱ እንዳይካሄድ ያደረጉ ሌሎች ምክንያቶች መሆናቸውንም አመልክተዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጠቅላላ ጉባዔው በተያዘው በጀት ዓመት እንዲካሄድ በወሰነው መሠረት ሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ. ም. 10ኛው ጠቅላላ መደበኛ ጉባዔ እንደሚካሄድ ገልፀዋል።
አዲስ የሚተካው አመራር በዓመታዊ መዋጮ፣ በኦዲት ሪፖርትና መሰል ጉዳዮች ላይ ከአባል ምክር ቤቶች ጋር ተወያይቶ አቅጣጫ እንዲያስቀምጥ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መወሰኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ውቤ መንግሥቱ በበኩላቸው፤ ቦርዱ ባለፉት ዓመታት በተቋም ግንባታ፣ የገቢ አቅምን በማሳደግ እንዲሁም የአባላት የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ላይ ስኬታማ ሥራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል።
በግሉ ዘርፍና በመንግሥት መካከል የበለጠ መቀራረብ ለመፍጠርና በጋራ ለመሥራት የሚያስችሉ መድረኮችም መካሄዳቸውንም ከተገኙ ውጤቶች መካከል እንደሚገኝበት ገልፀዋል።