ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ተግባራዊ ምላሽ እየሰጠች ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ተግባራዊ ምላሽ እየሰጠች ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን እያከናወነችና ተጨባጭ ውጤትም እያመጣች መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዕቅድ ትግበራ መርሃ-ግብር በዛሬው እለት ይፋ ሆኗል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ሚኒስትሮች፣ የፌዴራልና የክልል ተቋማት አመራሮችና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ወቅት፤ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለተከታታይ ድርቅና የጎርፍ አደጋ መጋለጧን አንስተዋል።
በተለይም ታዳጊ ሀገራትን በእጅጉ እየጎዳ ያለውን ይህንን ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ለመከላከል ጠንካራ ትብብር በመፍጠር መሥራት ይገባል ብለዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን አንስተው፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተለይም በአረንጓዴ አሻራ ልማት የተከናወኑ ስኬታማ ሥራዎችን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን እያከናወነችና ተጨባጭ ውጤትም እያመጣች መሆኑን ተናግረዋል።
በፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት መሠረት እስከ 2022 ዓ.ም የሚቆይ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የአየር ንብረት ለውጥ የምላሽ ዕቅድ ማዘጋጀቷንም ለአብነት አንስተዋል።
ለሚቀጥሉት 30 ዓመታትም የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እና የረዥም ጊዜ የአነስተኛ ካርቦን ልቀት የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ዕድገት ስትራቴጂ እንዳላትም ጠቅሰዋል።
በአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት አንዱ ምሰሶ ተደርጎ በመያዙ በዕቅድ እየተሰራበት መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ልማት የጎረቤት ሀገራትን አብሮ የመልማትና የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ መልኩ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።
ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ሕዝብን በማስተባበር ከ32 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል ዓለም አቀፍ ትጋቷን ማሳየቷን አስታውሰው፤ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር መሳካት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሏትን በርካታ ተግባራት በማከናወን ላይ ትገኛለች ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃም የሚጠበቅባትን ኃላፊነት ለመወጣትም በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ሀገራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዕቅዷን በማሻሻል ለተ.መ.ድ. የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፋዊ ስምምነት ከሁለት ዓመት በፊት ማስገባቷን አስታውሰዋል።
በተሻሻለው በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ትግበራ ዕቅድ፤ ኢትዮጵያ በ2022 ዓ.ም. የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን በ68 ነጥብ 8 በመቶ የመቀነስ ግብ ማስቀመጧን ገልፀዋል።
የትግበራ መርሃ-ግብሩ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሚናን በተቀናጀ መልኩ የመወጣት ቁርጠኝነትን የሚያሳይና የኢትዮጵያ ተምሳሌታዊ ጥረትን አጠናክሮ መቀጠል የሚያስችል ነው ብለዋል።
የመኸርና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መርሃ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ጉልህ አስተዋጽዖ እያበረከተ እንደሚገኝም አንስተዋል።
በኢነርጂ ዘርፍም ኢትዮጵያ ለታዳሽ የኃይል አማራጭ ትኩረት በመስጠት ግልጽ ስትራቴጂክ ፖሊሲ ነድፋ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።