አንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ ነቢይ መኮንን ከዚህ ዓለም በሞተ ተለየ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2016(ኢዜአ)፦አንጋፋው ጋዜጠኛ ገጣሚ፣ ተርጓሚና ደራሲ ነብይ መኮንን ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በዛሬው እለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡

ገጣሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን፤ “ስውር ስፌት” ቁጥር አንድና ሁለት፣ የግጥም መድብሎችን ጨምሮ በርካታ የግጥም ስራዎችን በተለያዩ መድረኮች በማቅረብ ይታወቃል፡፡

“የኛ ሰው በአሜሪካ” የተሰኘ የጉዞ ማስታወሻ መጽሐፉም ተጠቃሽ ስራው ነው፡፡

በማርጋሬት ሚሼል ተደርሶ፤ በመላው ዓለም ከፍተኛ ተነባቢነትን ያገኘውን “Gone With The Wind” የተሰኘውን ረጅም ልብ ወለድ መጽሐፍ “ነገም ሌላ ቀን ነው” በሚል ርዕስ ተርጉሞ አስነብቧል፡፡

የአዲስ አድማስ ጋዜጣን መስራች ከሆኑት አንዱ የሆነው ነቢይ መኮንን፤ ጋዜጣዋን በዋና አዘጋጅነት በመምራትና በርካታ መጣጥፎችን በማሳተም ተወዳጅ የስነ ጽሁፍ ስራውን አበርክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአንጋፋው ጋዜጠኛ ገጣሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን ህልፈት የተሰማውን ሃዘን በመግለጽ ለመላው ቤተሰቦቹ ወዳጅ ዘመዶቹና የሙያ አጋሮቹ መጽናናትን ይመኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም