በፖሊስ ተቋም ውስጥ በ2016 ዓ.ም በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
በፖሊስ ተቋም ውስጥ በ2016 ዓ.ም በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በፌዴራል ፖሊስ እንደ ተቋም በ2016 ዓ.ም በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም የማጠቃለያ ግምገማ በፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ማካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ ላይ ኮሚሽነር ጀነራሉ እንደገለጹት በወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ፣ በወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ፣ በአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያና በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ እንደ ተቋም በ2016 ዓ.ም በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል።
የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በየዓመቱ ሲንከባለሉ የመጡትን የምርመራ መዝገቦችን በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ እና በሀገራችን የፀጥታ ችግር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ የሽብርና ጽንፈኛ ኃይሎች የፈጸሟቸውን ወንጀሎች ተከታተሎ በከፍተኛ ዲሲፕሊንና በሙያዊ ብቃት መርምሮ ለህግ በማቅረብ ሰፋፊና አመርቂ ስራዎችን እንደሰራ ገልጸዋል።
እንደ ኮሚሽነር ጀነራሉ ገለጻ የተቋሙን አመራሮች አቅም ለማሳደግ በሀገራችን ፖሊስ ባልተለመደ መልኩ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል በውጭና በሀገር ውስጥ የተለያዩ ትምህርትና ስልጠናዎችን እንዲወስድ መደረጉን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በቴክኖሎጂ አቅምም ቀላል የማይባል እንደ ሀገርና እንደ አህጉር እምብዛም ያልተለመደ የቴክኖሎጂ አቅሞችን ወደ ኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ማምጣት መቻሉን ገልፀው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከሀገር አልፎ ለቀጠናው ጭምር ምሳሌ የሚሆን ስራዎች እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።