ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሐይማኖት አባቶች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሐይማኖት አባቶች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2016(ኢዜአ)፦ ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ የሐይማኖት አባቶች የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም ጥሪ አቀረቡ።
'የሀይማኖት ተቋሞቻችን ለዘላቂ ሰላማችን' በሚል መሪ ኃሳብ አገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በሠላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት በሚካሄደው የሰላም ኮንፍረንስ ላይ የሁሉም ቤተ-እምነት ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም በዚሁ ወቅት እንዳሉት የሃይማኖት አባቶች የኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አንድነት ለማረጋገጥ የላቀ አስተዋጽኦ አላቸው።
በአገሪቱ ከቂምና በቀል አስተሳሰብ የወጣ ትውልድ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የሐይማኖት አባቶች የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በተለያዩ ቦታዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች በንግግርና በውይይት እንዲፈቱና ዜጎች በሰላምና በነጻነት ወጥተው የሚገቡበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር የሐይማኖት አባቶችን ጥረት ይጠይቃል።
ሰላም በሁሉም ሐይማኖቶች አስተምሮ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሃይማኖት አባቶች ተከታዮቻቸውን በማስተማር ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ ነው።
ሰላም ከራስ የሚመነጭ እንደሆነ ያነሱት ሚኒስትሩ ሀገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ በየደረጃው ያሉ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረትና ትብብር እንደሚሻ ተናግረዋል።